የሩስያና ዩክሬንን ግጭት በተመለከተ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን በመደገፍ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም አላት - ኢዜአ አማርኛ
የሩስያና ዩክሬንን ግጭት በተመለከተ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን በመደገፍ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም አላት
ሀምሌ 20 ቀን 2014(ኢዜአ) የሩስያና ዩክሬንን ግጭት በተመለከተ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን በመደገፍ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እንደምታራምድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደረጉት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፤ በበኩላቸው የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የሩስያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም፣ የዩክሬንና ሩስያን ግጭትና ሌሎች የሁለትዮሽና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያና ሩስያ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ ባህል፣ በኢኮኖሚ ትብብር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሁለቱን አገሮች በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በስፋት መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተሰከሰተውን ግጭት በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በተመለከተም ለሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሶስቱ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን) በጀመሩት በመርህ ላይ በተመሰረተ ውይይት እንዲቋጭ ፍላጎት መኖሩንም አብራርተዋል።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሩስያ በትምህርት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመረጃና ደህንነት እንዲሁም በሌሎች ባለብዙ ዘርፎች በቀጣይ በሚኖራቸው ትብብር ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት ውስጣዊ መፍትሄ የሚያስፈልገው በመሆኑ ችግሩ በዘላቂነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ሩስያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሩስያና ዩክሬንን ጦርነት በተመለከተ ሰላማዊ አማራጮችን በመደገፍ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እንደምታራምድ ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካና ሩስያን የጠበቀ ግንኙነት ለማጠናከር በቅርቡ የሚካሄደው የአፍሪካ - ሩስያ የወዳጅነት ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ለዚህ መርሃ ግብር ተገቢውን ዝግጅት ታደርጋለች ብለዋል፡፡
በቅርቡ የሚካሄደው የአፍሪካ - ሩስያ የወዳጅነት ጉባኤም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፤ አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንዲችሉ አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት የአፍሪካውያንን መብት በማክበር መርዳት አለባቸው ለዚህ ደግሞ ከአፍሪካውያን ጎን እንቆማለንም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ