የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትውልዱን አዲስ ታሪክ ለመስራት ያዘጋጀ መልካም ጅምር ነው- የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትውልዱን አዲስ ታሪክ ለመስራት ያዘጋጀ መልካም ጅምር ነው- የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች
ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትውልዱን አዲስ ታሪክ ለመስራት ያዘጋጀ መልካም ጅምር በመሆኑ ሁላችንም ለስኬቱ በጋራ መቆም አለብን ሲሉ የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማሳካት ዜጎች በሁሉም አካባቢዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በመርሃ ግብሩ ባለፉት ሶስት አመታት ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን ለማልበስ ዘመቻው በተሳካ መልኩ ቀጥሏል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብርም "ዐሻራችን ለትውልዳችን" በሚል መሪ ሃሳብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እንቅስቃሴ ተጀምሮ እስካሁን 5 ቢሊዮን ተደርሷል።
የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎችም በዛሬው እለት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በመገኘት የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የመጀመሪያ ዙር የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበሩት የ98 አመት የእድሜ ባለጸጋው ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ፤ ችግኝ ከተከሉ የቀድሞ ተማሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለታሪክ የሚተላለፍና ለአገር የሚጠቅም ተግባር ፈፅመው እንዲያልፉ ያስቻላቸው መሆኑንም በመርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን እያፈራን እና ምቹ የማማሪያ አካባቢ እየፈጠርን ለአገራችን አስተዋፅኦ አድርገን ለማለፍ መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
''እኛ ዛሬ መጥተን ችግኝ መትከላችን እኔም ለትምህርት ቤቴና ለሀገሬ ይህንን አደርጋለሁ ብሎ የሚያስብ ዜጋ ለመፍጠር" ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትውልዱን የአዲስ ታሪክ ባለቤት የሚያደርግ መልካም ጅምር በመሆኑ ሁላችንም ለስኬቱ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ ትውልድና ሀገር የሚቀየረው ሁሉም ዜጋ መለስ ብሎ ሀገሩ ላደረገችለት ውለታ ተገቢውን ምላሽ ሲሰጥ ነው ብሏል።
እርሱም በቀድሞ ትምህርት ቤቱ አሻራውን በማኖሩ መደሰቱን ገልጸዋል።
የተፈሪ መኮንን የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ከ800 በላይ አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ወጪ በመቻል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያደረገ መሆኑንም ጠቁሟል።
የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ትምህርት ቤት ዲን ተሾመ ፈይሳ፤ በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ8 ሺህ በላይ ችግኞችን በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።
የቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የአሁኑ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ1917 ዓ.ም መመስረቱ ይታወቃል።