ቀጥታ፡

ከፊታችን አርብ ጀምሮ የሃይማኖት ተቋማት የሶስት ደቂቃ የምስጋና መርሃ ግብር ያካሂዳሉ

ሀምሌ 20/2014/ኢዜአ/ የሃይማኖት ተቋማት ከፊታችን አርብ ጀምሮ የሶስት ደቂቃ የምስጋና መርሃ ግብር እንደሚያካሂዱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የምስጋና መርሃ ግብሩ የሚካሄደው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ኢትዮጵያ ፈጣሪን ታመስግን'' በሚል ያስተላለፉትን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ ነው ብለዋል።  

መርሃ ግብሩ የሚካሄደው የሃይማኖት ተቋማቱን የምስጋና አስተምህሮ መሰረት በማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

በዚህም መሠረት የፊታችን አርብ በመላው ሀገሪቱ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከጁምአ ሰላት በኋላ የሶስት ደቂቃ የምስጋና ጸሎት እንደሚያካሂዱም ተናግረዋል።  

ቅዳሜ ደግሞ የአድቬንቲስት እምነት ተከታዮች በተመሳሳይ መርሃ ግብሩን የሚከውኑ ይሆናል።  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶችም በዕለተ እሁድ ከቅዳሴና ከአምልኮ መርሃ ግብሮቻቸው በኋላ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡ ይሆናል ነው ያሉት ።

የሃይማኖት ተቋማቱ መርሃ ግብሩን እንዲያስፅሙም ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም