በኢትዮጵያ የበሽታዎች ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የመከላከል ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የበሽታዎች ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የመከላከል ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ሀምሌ 20/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የበሽታዎች ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የመከላከል ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ፤ ወቅታዊ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኮቪድ 19፣የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ የወባ በሽታና በኩፍኝ ላይ በማተኮር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም የጤና ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ የኮቪድ ወረርሽኝ እንደ ጠፋ አድርጎ መታየቱ የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁመው ከሰኔ 17 እስከ ሀምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ብቻ 11 ሺህ ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው የ35 ሰዎች ህይወት ማለፉንም አስታውሰዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣን በተመለከተም በኢትዮጵያ እስካሁን በላብራቶሪ የተረጋገጠ ታማሚ እንዳልተመዘገበ አስረድተዋል።
በሽታውን የመከላከል ሥራዎች ከውጭ ሀገር በሚገቡ ተጓዦች እና ስደተኞችን ጨምሮ በድንበር መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ በሽታዎችና የወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የመከላከል ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ፤ የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሳህራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በርካቶችን እያጠቃ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑና 52 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በእነዚሁ አካባቢዎች የሚኖር በመሆኑ የወባ ወረርሽኝ እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል።
በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ወረርሽኝ መያዛቸውን አስታውሰው በተጠናቀቀው በጀት አመት ቁጥሩ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
የወባ ወረርሽኝ በተለይም በአማራ፣ ደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና ሌሎችም አካባቢዎች እየተባባሰ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የመመርመሪያ ኪቶች ስርጭትና የፀረ ወባ መድሃኒት ርጭት በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኩፍኝ ወረሽኝን በመከላከልም ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።