የአትሌቶቻችን ትብብርና የአሸናፊነት ጽናት በጋራ የመስራትን ውጤት በተግባር ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአትሌቶቻችን ትብብርና የአሸናፊነት ጽናት በጋራ የመስራትን ውጤት በተግባር ያሳየ ነው
ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአትሌቶቻችን ትብብርና የአሸናፊነት ጽናት በጋራ የመስራትን ውጤት በተግባር ያሳየ መሆኑን ኢዜአ ያነጋርናቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአሜሪካ አዘጋጅነት በኦሪገን ከተማ የተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት በውድድሩ ታሪክ ትልቁ ውጤቷ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በውድድሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባሳዩት ህብረት፣ ጽናትና የጋራ ስራ ሀገራችን 4 ወርቅ 4 ብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
የተገኘውን ድል በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
አቶ ታደሰ ላሚሎ እንዳሉት በተለያዩ የውድድር መድረኮች ላይ ባላቸው ተሳትፎ የማያሳፍሩን አትሌቶቻችን በዓለም ሻምፒዮናው ያሳኩት ውጤትና ያሳዩት ትብብር እጅግ አስደሳች ነው።
በውድድሩ አትሌቶች ያሳዩት ጽናትና የቡድን ስራ የሚያስመሰግን ከመሆኑ ባለፈ ያስመዘገቡት ውጤት ህዝቡን በጠቅላላ ያስደሰተና ሀገራዊ አንድነትን ያጠናከረ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አቶ ሁሴን ሻንቆና ወይዘሮ መሰረት ዓለሙ በበኩላቸው የተገኘው ድል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያኮራ መሆኑን በመናገር አትሌቶቹ ያሳዩት አንድነትና ህብረት ለሌሎችም አርዓያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ጀግኖች አትሌቶቻችን ሰንደቅ ዓላማችንን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው መላ ኢትዮጵያውያንን ስላኮሩ ትልቅ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ድሉ ህዝቡን ለመለያየት እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩትን የጠላቶቻችንንና ተላላኪዎቻቸውን ሀሳብ ቦታ በማሳጣት በአንድነት መስራት ከተቻለ ወደ ከፍታ ማማ መውጣት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው።
እንደ ሀገር ወደ ኋላ ሊጎትቱን የሚፈልጉ አካላትን በመታገል በአንድነት ጸንቶ መቆም ጊዜው የሚጠይቀው ቁርጠኝነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሀገር የተለያየ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ከችግር መውጫው መንገድ አንድነትና ለዓላማ በቁርጠኝነት መስራት መሆኑን የሚያመላከት ትልቅ ድል መሆኑን ነው የገለጹት።
በመሆኑም የአትሌቶቻችንን የትብብር፣ የጽናትና የአሸናፊነት መንፈስ ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሊደግመው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ተሳትፎ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት አትሌቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ የጀግና አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በዓለም ሻምፒዮናው የተሳተፉ አትሌቶችና ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላት ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።