ቀጥታ፡

አትሌቶች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ያደረጉበት መንገድ በአንድነት ከቆምን የማይታለፍ ፈተና እንደሌለ ማሳያ ነው--የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ (ኢዜአ) ሐምሌ 20/2014 "ጀግኖች አትሌቶች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ያደረጉበት መንገድ ተባብረን በአንድነት ከቆምን የማናልፈው ፈተና እንደሌለ ጥሩ ማሳያ ነው" ሲሉ በኮምቦልቻ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4 ወርቅ፣4 ብር እና 2 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያ በማምጣት ከአሜሪካ በመቀጠል ከዓለም 2ኛ በመውጣት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰይድ መንገሻ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ችግሩን ተቋቁሞ በአትሌቲክሱ ያስመዘገበችው ውጤት ብዙ ትርጉም አለው።

"በተለይ ብርቅዬ አትሌቶቻችን ሀገር በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ በቡድን ያደረጉት ትግልና የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪክ ሲወሳ ይኖራል" ብለዋል።

እንደ አትሌቶቻችን ተባብረን በአንድነት ከሰራን ሀገር የማታልፈው ፈተና እንደማይኖር የገለጹት አቶ ሰይድ፣ "በመተባብር ስኬት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ልጆች በተግባር አሳይተውናል" ብለዋል።

"በተገኘው ድል ኮርተናል፤ተደስተናል፤ ለአትሌቶቻችንና አስተባባሪዎቻቸው ትልቅ ክብር፣ አድናቆትና ምስጋናም አለን" ሲሉም ነው ነዋሪው የገለጹት።

"አትሌቶቻችን በቅንጅት በሀገር ፍቅር ወኔ የሰሩት ጀብድ ኢትዮጵያዊያን በችግር ውስጥ ሆነን በህብረት ከሰራን ዛሬም ውጤት ማምጣት እንደምንችል ያሳየንበት ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ጌቱ ሙጨ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።  

አትሌቶቹ ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ዳግሞ ከፍ ብላ ደምቃ እንድትታይ ያደረገ፤ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት ለማይፈለጉና ለእዚህም የሚሰሩ ጠላቶችን ያሳፈረ መሆኑን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ሴራ የማትፈርስ፣ በችግር ውስጥም ታሪክ መስራቷን የምትቀጥል ሀያል ሀገር መሆኗን በጀግኖች ልጆቿ አረጋግጣለች" ያሉት አቶ ጌጡ፣ እኛም ከአትሌቶቻችን በመማር አንድነትንና ሰላምን ጠብቀን ሌላ ድልና ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ ብለዋል።

አሁን ሀገር ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም እንደ አትሎቶቹ ሀገርን በማስቀደም ተባብሮና ተደጋግፎ መስራት ከተቻለ ነገም ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል   

ለእዚህም ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ውጤት በማስመዝገብ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በሁሉም መስክ እንዲሆን በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

"አትሌቶቻችን ህብረ ብሔራዊነታችንና ታላቅነታችንን ለዓለም በማሳየታቸው የተለየ ክብርና ምስጋና አለኝ" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን ናቸው።

የተገኘው ድል መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ያኮራ ከመሆኑ ባለፈ ኢትዮጵያዊያን በጥቃቅን ችግሮች የማንለያይና የማንበገር መሆናችንን ያረጋገጠ በመሆኑ በእጅጉ ተደስቻለሁ ብለዋል።

"እኛም አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን በሌሎች ልማቶች ታሪክ በመስራት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ወይዘሮ ዘሪቱ እንዳሉት ለኢትዮጵያ ከፍታ በተለይ የሴቶች አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ የእትሌቶች ስኬት አንድ ማሳያ ነው።

"ሴቶች በየትኛውም ዘርፍ ቢሰማሩ አንድነታቸውን አጠናክረው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉና ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ግንባር ቀደም መሆናቸውን ሌላ ማሳያ በመሆኑ ክብርና ምስጋና አለኝ" ብለዋል

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ድል እንደ አድዋ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለዓለም አቀፉ ዳግም ያረጋገጠና ታሪክ የሚዘክረው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም