ኢትዮጵያና ኬኒያ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኬኒያ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራረሙ
ሐምሌ 20 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያና ኬኒያ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት መፈራረማቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።
የኢትዮ- ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ድርድር በስምምነት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።
ስምምነቱን የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በተገኙበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዲሁም የኬንያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር ጎፌሪ ሙሊ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ አሁን ላይ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ የሚያስችላት ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እስከ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እያካሔደች የምትገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ከማድረጉም ባሻገር ፋይዳው የጎላ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ ያካሄደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት ፈርማለች፡፡
የግንባታ ሥራው በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከ183 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ መጠናቀቁን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳ፡፡