በክልሉ በህዝብ ጥያቄ በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ህዝቡ የሰላም እፎይታን አግኝቶ ወደልማት ገብቷል--አቶ ግርማ የሺጥላ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በህዝብ ጥያቄ በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ህዝቡ የሰላም እፎይታን አግኝቶ ወደልማት ገብቷል--አቶ ግርማ የሺጥላ
ባህር ዳር ሃምሌ 19/2014 ህብረተሰቡን በማወያየት በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ህዝቡ የሰላም እፎይታን አግኝቶ ወደ ልማት ሥራ መግባቱን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ገለጹ።
ሃላፊው በክልሉ የተካሄደውን የህግ ማስከበር ሥራ አስመልክቶ ዛሬ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፣ የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ በለውጥ ስርዓቱ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ በሚያወጡ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልገው አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ወደ ጦርነት ቢገባም በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ወረራውን መክቶ በመቀልበስ አበረታች ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዓለም ላይ በጦርነት ያሳለፉ አገራት በድህረ ጦርነት የውስጥ የጸጥታ ችግር እንደገጠማቸው ያመለከቱት አቶ ግርማ፣ በአማራ ክልልም የታጠቁ ሃይሎች በየቦታው ችግር መፈጠራቸውን አስታውሰዋል።
በዝርፊያና ስርቆት ተግባር በመሰማራት፣ ንጹሃንን በማገት፣ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና በሌሎች ህገ ወጥ ድርጊቶች ላይ በመሰማራት ክልሉንና ህዝቡን ሰላም ሲነሱ እንደነበረም ገልጸዋል።
ችግሩ እንዲፈታ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ብልጽግና ፓርቲ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ በተለያዩ መድረኮች ማወያየታቸውን የገለጹት አቶ ግርማ፣ ህዝቡ ሰላምና ደህንነት መታጣትን በግንባር ቀደምነት ማንሳቱን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ለውይይት ቅድሚያ በመስጠቱ ለጥፋት ከተሰለፉ አካላት ጋር ጭምር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል።
ይሁንና የተደረገው የሰላም ጥረትና ውይይት ፍሬ አልባ ሲሆን ክልሉ ወደባሰ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ መገባቱን ለምክር ቤቱ አስገንዝበዋል።
በህግ ማስከበሩ በተወሰደው እርምጃም አሁን ላይ የክልሉ ህዝብ የሰላምና ደህንነት እፎይታን በማግኘቱ ተረጋግቶ ወደልማት ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
"በክልሉ የተፈጠረው የታጠቀ ሀይል ስጋት ፈጥሮ ነበር" ያሉት አቶ ግርማ፣ በተወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ስጋቱ ቀርቶ ሰላም በመምጣቱ የክልሉ ህዝብ ደስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ሁለት ተቃርኖዎች እንደገጠሙት ጠቁመው፣ እነዚህም የአማራ ብሔርተኝነት እና የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ህዝብን መብት፣ ጥቅምና ልማት በማረጋገጥና ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የመገንባት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ወደብልጽግና ማማ ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም የክልሉ ህዝብ እንዲደግፍም አቶ ግርማ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ "የህግ ማስክበር ዘመቻው የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረገ፣ የህዝብን ይሁንታ ያገኘና በተገቢው ዝግጅት የተከናወነ ነው" ብለዋል።
ዘመቻው ክልሉ እንዳይረጋጋ የሚጥሩ ሃይሎችን በመለየት የተከናወነና ህዝቡ በነቂስ የተሳተፈበት መሆኑን ገልፀዋል።
በተወሰደው እርምጃም የክልሉ ህዝብ የልማት ሥራዎችን በተረጋጋ መንገድ እንዲያከናውን ለማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ "በቀጣይም የህግ ማስክበር ዘመቻው ህዝብን ባሳተፈ አግባብ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 3ኛ መደበኛ ጉባኤ 2ኛ ቀን ውሎው በአስፈጻሚ አካሉ ሪፖርት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።