ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሀምሌ 19 ቀን 2014 /ኢዜአ/ ዳያስፖራው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎትና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "በሀገራዊ ምክክር የዳያስፖራ ሚና እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፣ የዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች አንዲሁም ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ለተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ለመጣል እየተሰራ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ዳያስፖራው ባለፉት ጊዜያት በሀገሩ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን በመቃወምና ልማቷን በመደገፍ ትልቅ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋርም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንዲረዱ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ያብራሩት።

ዳያስፖራው በቀጠይም በሀገሩ ጉዳይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያካበተውን እውቀት እና ልምድ ወደ ተግባር እንዲቀይርም ይደረጋል ብለዋል።

በተለይም የተለያዩ ሀገራት ችግርቻቸውን በውይይትና በምክክር ለመፍታት ያደረጓቸውን ተሞክሮዎች በመቀመር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ቱባ የውይይትና የምክክር እሴቶች እንዳሏት የገለጹት አምባሳደር ብርቱካን፤ እነዚህን እሴቶች በማዳበር መጻኢ እድላችንን ብሩህ ልናደርግ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው መድረኩ ዳያስፓራው ስለ ሀገራዊ ምክክሩና ስለሀገሩ  ዓላማ በአግባቡ እንዲገነዘብ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ዳያስፖራው በሚኖርበት ሀገር ሆኖ ስለእናት ሀገሩ ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ እንዲኖረው በርካታ ውይይቶችን ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የሚኖርባቸውን አገራት ተሞክሮ በማካፈል ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው መድረኩ ስለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑና ስለተቋቋመበት ዓላማ ያላቸውን እውቀት እንዳሳደገው ጠቅሰው፤ በቀጣይ ኮሚሽኑ ለሚያደርጋቸው ውይይቶች አዎንታዊ ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የተለያዩ ሀገራት ችግሮቻቸውን በምክክር በመፍታት ያዳበሩትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም