ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናው ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ ነው...በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናው ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ ነው...በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር
ሐምሌ 19/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናውና የዓለም ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።
እስራኤል በኢትዮጵያ ግጭቶችን በሰላም አማራጭ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትደግፍም ነው ያረጋገጡት፡፡
መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሀገር ሽማግሌዎች በመላክ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየቱም እንዲሁ፡፡
አሁን ላይ ደግሞ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን፣ አለመግባባትና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነው።
ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት በሰላም አማራጭ ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ ሀገራቸው እስራኤል የሰላምንና የትብብርን አስፈላጊነት በአግባቡ ትገነዘባለች፤ ከዚህ አኳያ በዙሪያዋ ካሉ የዓረቡ ዓለም አገራት ጋር በቅርበት እየሰራች ነው ብለዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ለመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ቅርብ የሆነችው ኢትዮጵያ ችግሮችን በሰላም አማራጭ ለመፍታት እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
መንግሥት የጀመረው የሰላም አማራጭ ሂደት ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚጠቅም መሆኑን አንስተው፤ የሰላም አማራጩ ለጎረቤት ሀገራት፣ ለአፍሪካና ለቀጣናው አስተማሪ ነው ብለዋል።
እስራኤል የኢትዮጵያን የሰላም አማራጭ መንገድ እንደምትደግፍ ያነሱት አምባሳደሩ፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን መንግሥት ፊቱን ወደ ልማት ሙሉ ለሙሉ ለማዞር ያስችለዋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ሰላም ሲሰፍን ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የልማትና ሌሎችም ትብብሮች እንደሚያጠናክር ነው ያብራሩት።
"ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ ያደረገችና በሰላም አብረን እንኑር የምትል የሰላም ምልክት ናት" ያሉት አምባሳደር አለልኝ፤ በዓለም ሰላም ማስከበር ያላትን ሚናም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናውና የዓለም ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡