አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዓላማውን በማስተዋወቅ ሂደት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ትብብርና ተቀባይነት ማግኘቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዓላማውን በማስተዋወቅ ሂደት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ትብብርና ተቀባይነት ማግኘቱን አስታወቀ
ሀምሌ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኮሚሽኑ ዓላማውን በማስተዋወቅ ሂደት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ትብብርና ተቀባይነት ማግኘቱን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመመካከር የጋራ መግባባት ለመፍጠር በማለም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
የኮሚሽኑን የእስካሁኑን የሥራ እንቅስቃሴ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምክክር ኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ፤ ኮሚሽኑ ዓላማዎቹንና ሥራዎቹን በጥልቀት ለማስተዋወቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ከፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመገናኘት ዓላማውን አስተዋውቋል ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ከሰባት በላይ የክልል ርዕሰ-መስተዳድሮችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝቶ በመነጋገር ተመሳሳይ ተግባራት መፈጸሙን አስታውሰዋል።
የኮሚሽኑ አባላት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውረው ባደረጓቸው የትውውቅና ውይይት መድረኮች በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ከፍተኛ ትብብርና ተቀባይነት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይትም አብዛኞቹ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን አብረው ለመሥራት እና ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
ለአገራዊ ምክክሩ የበለጠ ጊዜ የሚወስደው የዝግጅት ምዕራፉ በመሆኑ የሚገባውን ትኩረትና ጊዜ በመስጠት ውጤታማ እንዲሆን ከሁሉም አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መላው ኢትዮጵያዊያን ኮሚሽኑን በመተባበርና በማገዝ እያሳዩት ያለውን መልካም ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሚያስተባብሩ 11 ኮሚሽነሮች ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰየማቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ