ቀጥታ፡

የክልሉን ሕዝብ የሥራ ባህል በማጎልበት የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት ይሰራል

ሀምሌ 19 ቀን 2014/ኢዜአ/ በአፋር ክልል የሕዝቡን የሥራ ባህል በማጎልበት የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሐጅ አወል አርባ ገለጹ።

ክልሉን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በአፋር ክልል በጦርነቱ ጉዳት በደረሰበት ካሳጊታ ተገኝተው ማዕድ የማጋራት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የቤት እድሳት አካሂደዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሐጂ አወል አርባ ካሳጊታ አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮ-ጂቡቲን ዋና መስመር የሆነችዋን ሚሌን ለመቆጣጠር አስቦ ከባድ ኪሳራ ያስተናገደበት ታሪካዊ ሥፍራ ነው ብለዋል።

ካሳጊታ የፌደራልና የክልል ፀጥታ ኃይሎች ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉበትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት አመራሩ ጠላት ከወረራቸው ሥፍራዎች ነጻ ማስወጣት ስለሚቻልባቸው ዕቅዶች መክረው ውሳኔ የተደረገባትም ሥፍራ እንደሆነች ገልጸዋል።

በጦርነቱ በክልሉ 28 ቢሊዮን ብር ውድመት መድረሱን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የአሸባሪው የሕወሓት ኃይል የትውልድ ጠላት መሆኑን በትምህርትና ጤና ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመትና የሰነድ ማስረጃ ማጥፋት እኩይ ተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

ክልሉን መልሶ ለማቋቋም የሕዝቡን የሥራ ባህል በማጎልበት የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዕለቱ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት ለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው፤ አገር ወዳዱ የአፋር ሕዝብና የፀጥታ ኃይል ኢትዮጵያን ከጠላት ለማዳን የፈጸሙት የአገር ጠባቂነት ተጋድሎ ኢትዮጵያዊያን ሲዘክሩት የሚኖር አኩሪ ገድል እንደሆነ ገልጸዋል።

መንግሥት አፋርን ጨምሮ በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ግንባታ የአምስት ዓመት ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማትም የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት አካል አድርገው በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ ለ300 ተማሪዎች የአንድ ዓመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በካሳጊታ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አሥር አዳዲስ መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ማቀዳቸውን  ገልጸዋል።

በቀጣይም በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም