በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እስካሁን ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እስካሁን ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል
ሐምሌ 19 ቀን 2014(ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እስካሁን ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።
በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር “አሻራችን ለልጆቻችን” በሚል መሪ ሀሳብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተከናወነ ይገኛል።
የመርሐግብሩን ክንውን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ የእስካሁኑ ሂደት ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ የመትከያ ሥፍራ መረጣ እንዲሁም የማኅበረሰብ ንቅናቄ ተከናውኖ ዘመቻው መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው መርሐግብር በተለይም ለአገር በቀል እጽዋቶች እንዲሁም ለደን ልማት የሚውሉ ዝርያዎች ትኩረት በመስጠት በመተከል ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለመትከል ከታቀደው 6 ቢሊየን ችግኝ እስካሁን 5 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን ዶክተር አደፍርስ ተናግረዋል።
የእቅዱን ግብ ለማሳካት እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ የችግኝ ተከላው እንደሚቀጥል አረጋግጠው የመጽደቅ መጠኑ ከፍ እንዲልም እንክብካቤው ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የደን ሽፋንን ከፍ ከማድረግ ባሻገር ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ከሚተከሉ ችግኞች 52 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ዝርያዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ አራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ይዛ እየሠራች መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ