ቀጥታ፡

በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ሰርጎ ለመግባት የሞከረውን አልሸባብ በመደምሰስ ተቆርጠው የቀሩ የሽብር ቡድኑን አባላት የማጽዳት እርምጃ እየተወሰደ ነው - ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው

ሐምሌ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ሰርጎ ለመግባት የሞከረውን አልሸባብ በመደምሰስ ተቆርጠው የቀሩ የሽብር ቡድኑን አባላት የማጽዳት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሃይል ስምሪት ሃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልና በምዕራብ ኢትዮጵያ የተወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ ሰላም የሰፈነ ሲመስላቸው ሰሞኑን በምስራቅ ኢትዮጵያ የማጥቃት ሙከራ ማድርጋቸውን ገልጸዋል።

የአልሽባብ አሸባሪ ቡድን በሶማሌ ክልል በአምስት ትናንሽ የጠረፍ አካባቢዎች ማለትም በየድ፣ አቶ፣ ኤልብርዴ፣ ዋቃሾና ፈርፈር ለማጥቃት ቢሞክርም በጸጥታ ሃይሉ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ጠቅሰዋል።

የሶማሌ ልዩ ሃይልና አመራርም የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ የነበረው ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 7 people and outdoors

የአልሽባብ ታጣቂዎች በአንድ አካባቢ ብቻ ሰርገው ገብተው የነበረ ቢሆንም የጸጥታ ሃይሉ ከበባ በማድረግ ከ100 በላይ የሽብር ቡድን አባላትን ደምስሷል ብለዋል።

ቡድኑ ለሽብር አላማው ሲጠቀምባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ ጠቅሰው፤ ተቆርጠው የቀሩ የሽብር ቡድኑ አባላትን የማጽዳት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ላይ በተወሰደው ርምጃ፣ መትረየስ፣ አር ፒ ጂ እና ሌሎች ከባድ የቡድን መሳሪያዎች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ተማርከዋል።

በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የሀገሩን ዳር ድንበር እያስከበረ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ፤ የሶማሌ ክልል ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለክልሉ ልዩ ሃይል ከፍተኛ የሞራልና የስንቅ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ጥምር የፀጥታ ሃይሉ ሙሉ በሙሉ በቀጣናው መግባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመድፈር የሚሞክሩ ሃይሎች ላይ ሙሉ ርምጃ ለመውሰድ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን ጨምሮ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም