ቀጥታ፡

ህገወጥ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ለብሔራዊ ፓርኮች ስጋት መሆኑ ተገለጸ

አዳማ መስከረም 5/2011 በሀገሪቱ የተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮች አካባቢ  ህገ ወጥ የተፈጥሮ ሀብት  አጠቃቀምና ጥፋት በፓርኮቹ የዱር እንስሳት ላይ ስጋት መደቀኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ። በኦሮሚያ፣አፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙት  ብሔራዊ ፓርኮችና  የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመታደግ ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንዳሉት በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚደርሰው የደን ጭፍጭፋ፣ሰደድ እሳት፣ህግ ወጥ ግጦሽ  ፣አደንና ሰፈራ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ አሳሳቢነቱ በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተጽፅኖ ማሳደሩ ነው፡፡ በኦሮሚያና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በሚገኘው አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ላይ ከሚፈፀመው ህገ ወጥ ሰፈራና አደን ባሻገር የአረም መስፋፋት ትልቁ ችግር መሆኑንም  አቶ ኩመራ አስረድተዋል። የዱር እንስሳት በተሽከርካሪ ጉዳት ሲደርስባቸው አጥፊዎችን በህግ ለመጠየቅና ተገቢውን ቅጣት ለመስጠት በህግ ማዕቀፍ የተደገፈ አሰራር ባለመኖሩ ችግሩን እንዳባበሰው ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት። በተመሳሳይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች  አዋሳኝ  የሚገኘው የአዳጌ አሰቦት ጥብቅ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ በሰዎች እየተፈጠረ ባለው የግጦሽና ሰፈራ መስፋፋት  እየተጎዳ መሆኑንም ጠቁመዋል። በፓርኮቹ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ህብረተሰብ አቀፍ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ አሰራርና አደረጃጀት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም በየአካባቢው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣አባገዳዎችና ዑጋዞችን ባሳተፈ መልኩ በመረባረብ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታውን ለመታደግ እየሰራን  መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አስረድተዋል። " አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ተገቢውን ክህሎትና ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ የፀጥታ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት ተባብረን እንሰራለን" ብለዋል። ብሔራዊ ፓርኮችን ከጥፋት ለመታደግ በህግ ማዕቀፍ የተደገፈ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት ህብረተሰቡን በባለቤትነት ያሳተፈ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ ያሳሰቡት  ደግሞ የኦሮሚያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ተወካይ አቶ አራርሳ ፈይሳ ናቸው። "የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ከሀገሪቱ የሥነ ምህዳር፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር በአግባቡ በመፈተሽ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አለብን" ብለዋል። የአፋር ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ተወካይ  አቶ ዳጌ አሊ በበኩላቸው በፓርኮች አካባቢ የሚኖረው አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ስለሀብቱ ጠቀሜታና አስፈላጊነት ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ችግሩን መፍታት ይጠበቅብናል ብለዋል። ችግሮቹን ለመፍታትም  የጋራ እቅድ ማዘጋጀትና ለተግባራዊነቱ ህብረተሰቡን በንቃት ባሳተፈ መልኩ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ከደንና አየር ንብረት ለውጥ ተቋማት የተወጣጡ  ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የዘርፉ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው  የምክክር መድረክ እየተሳተፉ ነው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም