ቀጥታ፡

የኢትዮ-እስራኤል ኢኖቬሽን ሳምንት ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ሐምሌ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮ-እስራኤል ኢኖቬሽን ሳምንት ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ይጀምራል።

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሳምንቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያለመ ኩነት መሆኑም ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ ኢትዮጵያ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ስታዘጋጅ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ከአምስቱ የእድገት ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ ተለይቷል ብለዋል፡፡

መሪ የልማት ዕቅዱን መሳካት ያለንን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የሌሎችን አገራት ተሞክሮ ወስደን ገቢራዊ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

May be an image of 1 person, sitting and standing

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እድገት መነሻ የሰው ሀብት ልማት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ከዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ አገሮች ተርታ ከምትመደበው እስራኤል ልምድ መውሰድ ታላቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮ-እስራኤል የኢኖቬሽን ሳምንት የእስራኤል የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያያሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ እስራኤል በማቅናት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተሻለ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥርዓተ-ምህዳር ለማንበር የሚያስችል አሰራር እውን እናደርጋለን ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ ኢትዮጵያና እስራኤል ከንጉስ ሰለሞንና ንግስተ ሳባ ዘመን የሚመዘዝ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው ብለዋል፡፡

May be an image of 1 person

እስራኤል በዓለም ቁንጮ ከሚባሉት በቴክኖሎጂ ከዳበሩ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ1948 ዓ.ም ነጻ ሀገር ሆና ከተመሰረተች በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም ከእስራኤል በመማር የሰው ኃይል ልማቷን በማሳደግ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ መድረስ ትችላለች ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከእስራኤል የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እድገት ትምህርት በመውሰድ ችግር ፈቺ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እውን ማድረግ የምትችልበት እድል እንዳላትም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና እስራኤል ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም