መንግስት ከዓለም ዓቀፍ የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ከዓለም ዓቀፍ የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር አመለከተ
ሐምሌ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ የደረሱ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያጣራ ያቋቋመው ዓለም ዓቀፍ የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመለከተ።
ኮሚሽንን በተመለከተ የተሠጠ መግለጫ መንግስት ከዚህ ኮሚሽን ጋር እንደማይተባበር ገልጾ እንደነበር አስታውሷል።
ሆኖም ከኮሚሽኑ አባላት እና ከሌሎች ባላድርሻ አካላት ጋር ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውይይቶች በተ.መ.ድ. የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚሽን ሃላፊነቱን ሲወጣ የመንግስትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም የአለም አቀፍ የሰብዐዊ መብት ስርዐት የብሄራዊ የህግ ስርዐቱ ደጋፊ እና ሟሟያ ሆኖ መታየት እንዳለበት አፅኖት የሚሰጠው እንደሆነ ጠቁሟል።
የአሟይነት መርህ (principle of complementarity) ባከበረ፣ ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች በነፃ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን ምርመራ የማይደግም እና መንግስት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በማያስተጓጉል መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ በዝርዘር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ማዕቀፍ (modalities of engagement) ላይ መስማማት ከተቻለ ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር ገልጿል።
በዚህም መሠረት በጄኔቫ የተጀመሩ ውይይቶችን ለመቀጠል የባለሞያዎቹ ኮሚሽን አባላት በአዲስ አበባ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችን እና አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ ይገኛሉ ሲል መግለጫው አመልክቷል።
የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽንን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሠጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ የደረሱ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያጣራ ያቋቋመው ዓለም ዓቀፍ የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን ከአገራችን ጋር የትብብር እድልን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ በአዲስ አበባ ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ የደረሱ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ የባለሞያዎች ኮሚሽን አቋቁሟል።
የኢፌዲሪ መንግስት ይህ ኮሚሽን የተቋቋመበት ሂደት እና የተሰጠው ሃላፊነት ግልፅነት የጎደለው፣ ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ቅኝት ያለው እና ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን የሰብዐዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲሁም የዚህም የጥምር ምርመራ ቡድን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተገቢው መልኩ ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ በመጠቆም ተቃውሞውን ገልፆ እንደነበር ያታወሳል።
በዚህም መሠረት መንግስት ከዚህ ኮሚሽን ጋር እንደማይተባበር ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
ሆኖም ከኮሚሽኑ አባላት እና ከሌሎች ባላድርሻ አካላት ጋር ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውይይቶች በተ.መ.ድ. የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚሽን ሃላፊነቱን ሲወጣ የመንግስትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም የአለም አቀፍ የሰብዐዊ መብት ስርዐት የብሄራዊ የህግ ስርዐቱ ደጋፊ እና ሟሟያ ሆኖ መታየት እንዳለበት አፅኖት የሚሰጠው የአሟይነት መርህ (principle of complementarity) ባከበረ፣ ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች በነፃ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን ምርመራ የማይደግም እና መንግስት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በማያስተጓጉል መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ በዝርዘር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ማዕቀፍ (modalities of engagement) ላይ መስማማት ከተቻለ ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር ተገልፆል።
በዚህም መሠረት በጄኔቫ የተጀመሩ ውይይቶችን ለመቀጠል የባለሞያዎቹ ኮሚሽን አባላት በአዲስ አበባ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችን እና አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤