ቀጥታ፡

የአሰብና የምጽዋ ወደቦችን በማልማት ወደ ስራ እንዲገቡ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 5/1/2011 የአሰብና የምጽዋ ወደቦችን በማልማት ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት አመታት ያክል ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት ወደ ሰላም በመመለሱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አገሮቹ አብረው ለመስራት መስማማታቸው ይታወቃል። በዚህም አገሮቹ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ፣ በትራንስፖርት፣ በድንበር ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድ እንዲሁም በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን የሰላም ግንኙነት ለማጠናከር ሁለቱም አገሮች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአሰብንና የምፅዋን ወደብ ለመጠቀም የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ ተናግረዋል። በዚህም በአጠቃላይ ወደቦቹን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚመለከት በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።  ለዚህም የአሰራር ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እንደ መንገድ፣ የሆቴሎች፣ የባለሙያዎችና ሌሎችንም አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል። በቀጣይ በሁለቱም አገሮች በኩል ለዝግጅት የተሰሩ ስራዎችን በማቀናጀት ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች የሚመሩበት የስምምነት ማዕቀፍ እንደሚኖር ገልጸዋል። እቃዎች የሚተላለፉባቸውና የሚከማቹባቸው ደረቅ ወደቦችን ከማዘጋጀት አንጻር አዋጭ የሆኑ የአገር ውስጥ ደረቅ ወደቦችን የማስፋፋትና የማልማት ስራዎችን ማከናወን ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ነው የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ የአሰብና ምጽዋ ወደቦችን የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በቅርቡ የአሰብና የምጽዋ ወደቦችን መጠቀም የሚያስችላት ቁመና ላይ መሆኗን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። በመጀመሪያውና በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች መሰረት ኢትዮጵያ በአጎራባች አገሮች ወደቦች ጂቡቲ 60 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ጭነት ስታስተናግድ፣ በርበራ 30 በመቶ እንዲሁም የሱዳን ወደብ 10 በመቶ ያስተናግዳሉ ተብሎ በእቅድ ደረጃ ተቀምጧል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኤርትራ በኩል የአሰብና የምጽዋ ወደቦችን ለመጠቀም አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ወደቦቹ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም