ጀርመን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ስቴፈን አዎር - ኢዜአ አማርኛ
ጀርመን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ስቴፈን አዎር
ሐምሌ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)ጀርመን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር አስታወቁ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያና ጀርመን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውን ገልፀው፤በኢትዮጵያ በሴቶች፣ወጣቶች፣አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ዙሪያ እየተሰሩ ላሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስኬታማነት የጀርመን መንግሥት የበኩሉን እገዛ ሲያደርግ መቆየቱንም አውስተዋል።
እንደ ሀገር ለሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ጥረት የጀርመን መንግሥት ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።
አምባሳደር ስቴፈን አዎር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሴቶችን በማብቃት ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ እንዲሁም ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰፊው እንዲሰማሩ ለማስቻል እየተከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ከሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የማህበራዊ ስነልቦና ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት እያደረገው ያለውን ጥረትም ማድነቃቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡
ጀርመን በቀጣይም በሰላም ግንባታ፣ሴቶችን በማብቃት፣ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ፣በታዳሽ ኃይል አቅርቦት በሌሎችም መስኮች ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ተግባራት ውጤታማነት የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ