ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሊከፋፍሉት የሚሰሩ አካላትን ፍላጎት ማክሸፍ አለበት-ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሊከፋፍሉት የሚሰሩ አካላትን ፍላጎት ማክሸፍ አለበት-ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ
ሐምሌ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሊከፋፍሉት የሚሰሩ አካላትን ፍላጎት ማክሸፍ እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በአዲስ መልኩ ስራ የጀመሩት የመጅሊሱ አመራሮች የሙስሊሙን አንድነት ለማጠናከር ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
ኢዜአ በጽህፈት ቤታቸው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ፤ ህዝበ-ሙስሊሙን አንድ አድርጎ የሚመራ ጠንካራ ተቋም መገንባት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የረዥም ጊዜ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበረው ስርዓት ይህ ጥያቄ እንዲመለስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈሉም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ አኳያ ለረዥም ጊዜ ህዝበ-ሙስሊሙን አንድ ለማድረግ የተሞከሩ በርካታ ጥረቶች ሊሳኩ አለመቻላቸውን አስታውሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት መንግስት የሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ እንዲመለስ የሚጠበቅበትን እገዛ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሁሉንም ክልሎች ያሳተፈ ምርጫ በማካሄድ የራሱን አመራሮች በመምረጥ በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈት መቻሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እስልምናን ከተቀበሉ ቀደምት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሚመጥን መልኩ ጠንካራ መጅሊስ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
አንድነት ኃይልና ሰላም መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በአዲስ መልኩ ስራ የጀመሩት የመጅሊሱ አመራሮች የሙስሊሙን አንድነት ለማጠናከር ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት፡፡
ከዚህ ቀደም በርካታ ኡለማዎች ጊዜ ሰጥተው ያዘጋጁት "የአንድነትና ትብብር" ሰነድ ቢኖርም እስካሁን ወደ ተግባር አለመለወጡን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ የሚፈለገው አንድነትና ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
"የመጅሊሱ አመራሮች ሰነዱን ወደ ተግባር ለማስገባት ይሰራሉ" ሲሉም አመልክተዋል።
ሆኖም አንዳንድ አካላት የተለያዩ የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝበ-ሙስሊሙን ለመከፋፈል እየሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ሸኽ ሀጂ ኢብራሒም፤ የእነዚህ አካላት ዋነኛ ፍላጎት ሙስሊሙን በመከፋፈል ሀገር ማተራመስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ህዝበ-ሙስሊሙ ይህን ተገንዝቦ አንድነቱን ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባም ጥሪ አቅርበው፤ በየትኛውም ጊዜ የሚፈጠሩ ችግሮችን ተቀራርቦ በውይይት መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤