ዛሬ ማለዳ በምናለሽ ተራ አካባቢ የተከሰተ የእሳት አደጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሐምሌ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምናለሽ ተራ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር መዋሉን የከተማዋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ ከተለዩ የገበያ ማዕከላት አንዱ መሆኑን በመግለጽ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
የኢዜአ ሪፖርተር አደጋው በደረሰበት በአካባቢ ተዘዋውሮ ለመታዘብ እንደሞከረው አደጋው በኤሌክትሪክና መሰል እቃዎችን መሸጫ ሱቆች ላይ ነው የተከሰተው።
የጸጥታ ኃይሎች የእሳት አደጋው የደረሰበትን ስፍራ ከተሽከርካሪና እሳቱን በማጥፋት ሂደት ከሚሳተፉ ሰዎች ውጪ ነጻ በማድረግ እሳቱን የማጥፋት ስራ ተከናውኗል።
በተጨማሪም በአካባቢ በወትሮው የሚታየው የንግድ እንቅስቃሴ ያለምንም ስጋት እንዲከናወን የጸጥታ ሃይሎች ሲሰሩ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ዛሬ ማለዳ 1:06 ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታዉ ምናለሽ ተራ በሚገኙ ንግድ ሱቆች ላይ የእሳት አደጋ አጋጥሟል።
አቶ ንጋቱ እንዳሉት ለኮሚሽኑ የአደጋው ጥሪ እንደደረሰ ከቅርንጫፍ ጣቢያዎቻችን ዘጠኝ የእሳት አደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎችና 70 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እንዲሰማሩ ተደርጓል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋር በአደረጉት ከፍተኛ ርብርብ የእሳት አደጋዉን በአጭር ሰአት መቆጣጠር ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህ ሂደትም እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት 108 ሺህሊትር ዉሀ ጥቅም ላይ ውሏል ያሉት አቶ ንጋቱ አካባቢዉ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ የሚያጋጥምበትና በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ ከተለዩ የገበያ ማዕከላት አንዱ ነዉ ብለዋል።
በአደጋው በሰዉ ላይ ምንም አይነት የደረሰ ጉዳት የለም በማለት ያስረዱት ባለሙያው የጸጥታ ሀይሎችም በቦታዉ ፈጥኖ በመድረስ ድጋፍ አድርገውልናል ሲሉ ምሰጋናቸውን አቅርበዋል።
በእሳት አደጋው በንብረት ላይ የደረሰውን አደጋና መታደግ የተቻለውን ሀብት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ እንደደረሳቸው እንደሚገለጽም አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ምንአለሽ ተራ በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ ከተለዩ የገበያ ማዕከላት አንዱ መሆኑን በመግለጽ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም