የጀግናው እሸቴ ሞገስና የልጁ ይታገሱ እሸቴን ግለ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጀግናው እሸቴ ሞገስና የልጁ ይታገሱ እሸቴን ግለ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ተመረቀ
ሐምሌ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጀግንነት የተሰውትን የጀግናው እሸቴ ሞገስና የልጁ ይታገሱ እሸቴ ግለ ታሪክ የያዘ “ሞትን ያስበረገጉ ጀግኞች” መጽሐፍ ተመረቀ፡፡
ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት፤ ከክብሯ ዝቅ እንዳትል ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው በዘመናት መካከል ነጻነቷን ያስጠበቁ እልፍ አዕላፍ ልጆች አሏት።
ልጆቿ ለክብሯ ዘብ ሆነው ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ ቅኝ ገዢዎችን በልበ ሙሉነት ተፋልመው ድል በመንሳት ዓለምን አስደምመዋል፤ ለመላው ጥቁር ህዝብም የነጻነት ምልክት ሆነዋል።
በውስጥም ለጥቅማቸው የተገዙ ሆድ አደሮች የእናታቸውን ጡት ለመንከስ ሲዳዳቸው እምቢኝ በማለት ጀግኖች ልጆቿ ለክብሯ መስዋእትነት ከፍለዋል።
ታሪክ ከማይዘነጋቸው ጀግኖች ልጆቿ መካከል አሸባሪውን የህወሃት ቡድን በመፋለም በጀግንነት የተሰውት አባትና ልጅ እሸቴ ሞገስና ይታገሱ እሸቴ ይጠቀሳሉ።
ጀግኖቹ እሸቴ ሞገስና ልጁ ይታገስ እሸቴ ለአገር ነፃነትና ለወገን ክብር ሲሉ የህወሃት ወራሪ ኃይልን በመፋለምና በትንሹ 9 አሸባሪዎችን በመግደል በክብር መሰዋታቸው ይታወሳል።
የነዚህን ጀግኖች ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳ ዘንድም የጀግናው እሸቴ ሞገስና የልጁ ይታገሱ እሸቴን ግለ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ስነስርአቱም የጀግኖቹን ቤተሰቦች ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው ደራሲያንና ምሁራን ተገኝተዋል።
የመጽሐፉ ደራሲ ካፒቴን አልዓዛር አያሌው እነዚህን ጀግኞች ለማስታወሥና ገድላቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ መፅሐፉን ለመፃፍ መነሳሳታቸውን ተናግረዋል።
ደራሲው የጀግናው አርበኛ እሸቴ ሞገስና የልጁ ይታገሱ እሸቴ ግለ ታሪክ ለሌሎች በርካታ ጀግኖች መታሰቢያ ነው ብለዋል።
በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የጀግናው እሸቴ ወንድም ዶክተር ይተብቱ ሞገስ በበኩላቸው መጽሐፉ የሁለቱ ጀግኖች ታሪክ ለሌሎች በርካታ ወጣቶች አርአያ እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ጀግኞች ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያውያን አንድነት በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል እንጂ ሀገር መቼም ቢሆን አትፈርስም ብለዋል።
ለመጽሐፉ ህትመት የድርሻቸውን ለተወጡ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው እነ እሸቴ ሞገስ ያሳዩት ገድል ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ፍቅር ያላቸውን ቦታ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በደራሲ ካፒቴን አላዛር አያሌው የተጻፈው “ሞትን ያስበረገጉ ጀግኞች” በሚል ርዕስ የተጻፈው ይኸው መጽሀፍ 520 ገፆች አሉት።
ጀግናው እሸቴ ሞገስና ልጁ ይታገሱ እሸቴ ህዳር 17 2014 በሸዋ ሮቢት አካበቢ በምትገኘዋ ሳላይሽ በምትባል ስፍራ ከህወሃት ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ፍልሚያ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ታሪክ ሰርተው በጀግንነት የተሰውት አባትና ልጅ አስከሬን ጥር 01 ቀን 2014 ዓ.ም በክብር የማሳረፍ ስነ ስርአት በሸዋሮቢት ከተማ መካሄዱም እንዲሁ።