የእንስሳት ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው--ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው--ሚኒስቴሩ
ሶዶ፤ ሐምሌ 17/2014 (ኢዜአ) የእንስሳት ተዋፅዖ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴርና የደቡብ ክልል ስራ ሀላፊዎች በወላይታ ዞን በእንስሳት ዝሪያና በመኖ ልማት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ጎብኝተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደገለጹት ሀገሪቱ ያላት የእንስሳት ሀብት አቅም ከፍተኛ ቢሆንም ዝሪያ ማሻሻልና የአያያዝ ክፍተቶች በስፋት ይስተዋላሉ።
ክፍተቶቹን በአግባቡ በመለየት በዕውቀትና በምርምር በታገዘ መልኩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የእንስሳት መኖ ልማትን በማሳደግና የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማዳቀል ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
የእንስሳት ተዋፅዖ ምርትን ለማሳደግ የመኖ አቅርቦት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት መሰራቱን ዶክተር ፍቅሩ አስረድተዋል።
የስራ ሀላፊዎቹ በወላይታ ሶዶ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሚገኘውን የዶሮ፤ የሀር ትልና ሌሎች የእንስሳት መኖ ልማት በከተማው የሚገኘውን የደቡብ ክልል የዳልጋ ከብቶች ዝሪያ ማሻሻያ ማዕከልና በማራ ጫሬ ቀበሌ በአርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የለማ የመኖ መገብኘቱ ሂደቱን ለመገምገመ ያለመ ነው ብለዋል ።
"በቦረና አካባቢ በተከሰተው ድርቅ እንስሳቶቹን ወደ ወላይታ አከባቢ በማምጣት ከድርቁ ባሻገር ዝሪያቸውን ለማቆየትና ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በተሰራው የማዳቀል ስራም የተሻለ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው የእንስሳት ተዋፅዖ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የዝርያ አቅርቦት እጥረት ማነቆ መሆኑን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ የተጀመረው በተፈጥሮ፣ በሰው ሰራሽና በባዮ ቴክኖሎጂ መንገድ ከፍተኛ ምርት ከሚሰጡ ዝርያዎች ጋር የማዳቀልና የማስፋፋት ስራው ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የእንስሳት ተዋፅዖ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሂደት የእንስሳት አርቢዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ዶክተር አስራት በተለይ ወጣቶች የእንስሳት እርባታ ስራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእንስሳት ተዋፅዖ ምርት ማደግ የስነምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የስራ እድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በተለይ እንደ ወተት ያሉ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የሀገር ውስጥ ምንዛሬ ለማሻሻልም የሚረዳ መሆኑን አመልክተዋል።
የእንስሳት ዘርፍን በአግባቡ በመያዝና ዝሪያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ጉድለት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ናቸው።
በመሆኑም ከእንስሳት ሀብት ልማት ጨምሮ ከሁሉም ዘርፎች ተገቢውን ውጤት ለማግኘት ታልሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ57 ሺህ በላይ የከብቶች ዝርያ መሻሻሉን ገልፀዋል።
ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም መሬት ላይ ለእንስሳት ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ሚና ያላቸው የመኖ ልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የእንስሳት ማሻሻል፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት ማሳደግና እንዲሁም የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽነት የማስፋት ስራ ውጤት በሚያስገኝ መልኩ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት።