ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችና ስምምነቶች መሰረት መብቷን በአግባቡ ለመጠቀም እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችና ስምምነቶች መሰረት መብቷን በአግባቡ ለመጠቀም እየሰራች ነው
ሐምሌ 17/2014 /ኢዜአ / ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችና ስምምነቶች መሰረት መብቷን በአግባቡ ለመጠቀም እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ።
አትዮጵያ ከአገራት ጋር ካላት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በተጨማሪ በዓለም ዓቀፍ የባህር ሕጎች እየተጠቀመች መሆኑም ተገልጿል።
በማሪታይም ባለሥልጣን የማሪታይም አስተዳደር ተጠባባቂ ዳይሬክተር ካፒቴን ጌትነት አባይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የባህር በር አልባ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል ዋነኛው በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት የተደረሰው ስምምነት ሲሆን በአንቀጽ 125 ላይ የባህር በር አልባ አገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ድንጋጌ መኖሩን ያነሳሉ።
በአንቀጹ መሰረት የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ ካለበት ቦታ መድረስ እና የመመለስ መብት ሰጥቷቸዋል።
ይህ ስምምነት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውና 'የባህር ሕጎች ሁሉ እናት' ተብሎ ጭምር የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ስምምነቱ ወደብ አልባ አገራት በስፋት እየተጠቀሙበት ቢሆንም ወሳኙ ነገር በአገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት መሆኑንም ያነሳሉ።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የባህር በር ባላቸው የጎረቤት አገራት አማካኝነት ንግዷን ለማቀላጠፍ በዲፕሎማሲያዊ መንገድም ይሁን በሕጎቹ መሰረት እየተጠቀመች ትገኛለች ብለዋል።
ወደፊትም በርከት ያሉ የባህር በር ያላቸው አገራት ወደቦችን ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አስታውሰዋል።
በማሪታይም ባለሥልጣን ዓለም አቀፍ የማሪታይም ሕግ ጉዳዮች አማካሪ አነኔ ቀጄላ እንዲሁ፤ ሕጎቹና ስምምነቶቹ ያለምንም ገደብ ባህር መድረስን የሚፈቅዱ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያም ከአገራት ጋር ባላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችና ስምምነቶች መሰረት በጂቡቲ፣ በሱዳንና በበርበራ በኩል የባህር በር ተጠቃሚ መሆኗን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል እነዚህ ሕጎችና ስምምነቶች በርካታ ጥቅም ቢሰጡም ኢትዮጵያ ወደብና ባህር ትራንስፖርት ብቻ እየተጠቀመች ትገኛለች ብለዋል።
ሕጎቹና ስምምነቶቹ ግን ባህር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሀብቶችን ጭምር መጠቀም የሚፈቅዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወደፊት ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ከገነባች በኋላ እነዚህንም መብቶች ለመጠቀም መንቀሳቀስ እንደምትችል አንስተዋል።
ኢትዮጵያ አብዛኛው ዓለም አቀፍ ንግዷ የሚከናወነው በጂቡቲ በኩል ቢሆንም የሌሎች አገራት ወደቦችንም እየተጠቀመች መሆኑ ይታወቃል።
እስካሁን ካለው በተጨማሪ የኬንያና የሶማሊያ ወደቦችን የመጠቀም እድል እንዳላትም የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አመላክቷል።