ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ገለጸ

ሐዋሳ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) 17 በመቶ ላይ የሚገኘውን ሀገራዊ የደን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶገነት የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ጋር በመተባበር በምርምር የታገዘ የደን ልማት ቦታ ላይ ትናንት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ከ54 ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ መሬት መራቆቱን በጥናቶች ተመላክቷል።

የተራቆቱ አካባቢዎችን በፍጥነት ተንከባክቦ ማዳንና ምርታማ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ገልጸው፤ የተራቆተ መሬትን በእጽዋት የማልበስ ስራ መስፋፋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ደን እና እጽዋትን ላይ የተመሰረተ ልማት የአካባቢ መራቆትን እንደሚከላከል፣ የግድቦችን ውሃ የመያዝ አቅም እንደሚጨምርና ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸው፤ የእጽዋት ልማትን ማጠናከር የደን ሀብትን የገቢ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በዓመት ከ130 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ እንጨት ለማገዶና ለግንባታ ስራዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል ጠቅሰው፤ የደን ልማትን ማጠናከር ከፍተኛ የሆነውን የማገዶና የግንባታ ግብዓት ፍጆታ እና ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ይህንን ፍጆታ የደን ልማትን በማጠናከር ማካካስ ካልተቻለ የተፈጥሮ ሀብትን በማውደም የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እንዲባባስ ያደርጋል ብለዋል።

በመሆኑም የደን ሽፋንን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ 17 በመቶ ላይ የሚገኘውን የደን ሽፋን በ10 ዓመታት ውስጥ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለዕቅዱ መሳካት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ በበኩላቸው የደን አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የተፈጥሮ ደኖችን በዘፈቀደ ለእርሻ ስራ እና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ከማዋል በመቆጠብ እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህንን ለመከላከል የህግ ማእቀፍ በማዘጋጀት ህብረተሰቡ የደን ሀብቱን በመንከባከብ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ተዘርግቶ ውጤት እንደመጣ ጠቅሰዋል።

በደን ልማት ላለፉት 44 ዓመታት ባለሙያዎችን በማፍራት አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የወንዶ ገነት የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተወካይ ዶክተር ሽመልስ ንጋቱ፤ ኮሌጁ የሀገሪቱን የደን ሀብት ቆጠራ በመምራት እና በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከመማር ማስተማሩ ስራ ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲቀላጠፍ በዋናነት ሀገር በቀል የችግኝ ዝርያዎችን በማፍላትና ለተለያዩ አካላት በማሰራጨት ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም