ብሔራዊ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት በጥራት አስተዳደር ስርዓት ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

ሐምሌ 17 ቀን 2017 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት በሲስተም ሠርተፍኬሽን የጥራት አስተዳደር ስርዓት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ገለጸ።
አግልግሎቱ ለተገኘው ዓለም አቀፍ የጥራት አስተዳደር ሚና ለነበራቻው ባለሙያዎችና አመራሮች በአዳማ ከተማ እውቅና ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት ተሰማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የተገኘው የጥራት አስተዳደር እውቅና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳለጥ፣የንግድ ደረጃን ለማዘጋጀት ወሳኝ ነው።
በተለይ የ(አይ ኤስ ኦ) ደረጃን ያሟሉ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ብቃትና የምርት ጥራት ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችል እውቅና መገኘቱን አመልክተዋል።
የእውቅናው መገኘት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት የሚያሳካ ከመሆኑንም ባለፈ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ በማኑፋክቸሪንግና የግብርና ምርቶች ጥራት ተወዳዳሪ እንድትሆን ሰፊ እድል የሚሰጣት መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ምርት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቀባይነትና የገበያ መዳረሻዎችን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
እስካሁን 104 ለሚሆኑ ተቋማት ዓለም አቀፍ የጥራት እውቅና መስጠት መቻሉን የገለጹት ተጠባባቂ ዳይሬክተሯ የጥራት ስርዓቱን ጠብቀው መጓዝ ያልቻሉ 36 ተቋማት የእውቅና አግልግሎቱን መነጠቃቸውንም ተናግረዋል።
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም ባንክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወንደሰን ፍሰሃ በበኩላቸው ተቋሙ ያገኘው እውቅና በስነ ልክና በአክሪዲቴሽን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ለምናመጣው ውጤት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም