ሀገር በቀል ዕጽዋቶችን ለመጠበቅና ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው

ሆሳዕና ሀምሌ 17/2014 (ኢዜአ)  በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ሀገር በቀል እጽዋቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ አስተዳደር በተረከበው ከ12 ሄክታር በላይ መሬት ላይ "የዕጽዋት አጸድ ማዕከል" ፕሮጀክት ቀርጾ ሀገር በቀል ችግኞችን ማፍላትና ማልማት ጀምሯል።

ፕሮጀክቱ ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ከመስጠትና ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ውበትና ሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመላክቷል።

የኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ለአረንጓዴ ልማት በነበረው አነስተኛ ትኩረት በኢትዮጵያ የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ህዝብን በማስተባበር በተሰራው የአረንጋዴ ልማት ሥራ የደን ሽፋኑ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

"ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የእፅዋት ሽፋን ማሳደግና በእዚህ ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን በተጨባጭ የመደገፍ ዓላማ አለው" ያሉት ዶክተር ፈለቀ፣ ለእዚህም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ችግኝ የማፍላትና አረንጓዴ ልማትን የሚያግዙ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ኢንስትቲዩቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን በላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እየተከለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዶክተር ፈለቀ አክለውም ኢንስትቲዩቱ በመጥፋት ላይ ያሉና ለሀገር ከፍተኛ ገቢ በማስገባት ረገድ ጠቀሜታ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን እያስፋፋና እየጠበቀ ነው።

ለእዚህም መዓዛ እና መድሃኒትነት ያላቸው እንዲሁም ለውበት የሚሆኑ ችግኞችን ለማስፋፋትና ለመጠበቅ የሚያስችል ፕሮጀክት በተለያዩ አካባቢዎች ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ለመድሀኒትነት፣ ለውበት እንዲሁም ለተለያየ ጠቀሜታ የሚውሉ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመጠበቅና ለማስፋፋት አስተዋጽኦ ያለውን የእፅዋት አፀድ ማዕከከል ኢኒስቲትዩቱ በተለያዩ አካባቢዎች መክፈቱንም ጠቁመዋል።

እስካሁን ጉለሌ፣ በወንዶ ገነትና በደብረ ዘይት የተከፈቱ ማዕከላት ሥራ መጀመራቸውን ገልጸው፣ አራተኛው የእፅዋት አፀድ ማዕክል ፕሮጀክት በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ ከ12 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ተከፍቶ ወደስራ መግባቱን አስረድተዋል።

በኢኒስቲትዩቱ የእጽዋት ተመራማሪ አቶ ኃይሉ እድሉ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በመጥፋት ላይ ያሉ እፅዋቶችን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማሰባሰብ ዘላቂነታቸውን ማስቀጠል የማዕከሉ አንዱ ተግባር ነው።

በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ከሾኔ ከተማ አስተዳደር በወሰደው 12 ሄክታር በላይ መሬት የዕጽዋት ማዕከል በመክፈት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በዘርፉ ለሚማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለማስተማሪያነትና የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ኃይሉ እንዳሉት ማዕከሉ እስከአሁኑ ድረስ ለ20 የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደስራ ሲገባ ከ150 በላይ ዜጎች በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋል።

የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ተመስገን ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በማጠናከረ በኩል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በአካባቢው የደን ሽፋንን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ህብረተሰቡ ለሀገር በቀል እፅዋት ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል

እንደ ከንቲባ መስፍን ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ምቹ መደላድል ይፈጥራል።

"ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራና ተጨማሪ ዕድሎችን ይዞ ስለመጣ ከተማ አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩሉን ይወጣል ብለዋል" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ፕሮጀክቱ በጥበቃ የሥራ እድል ማግኘታቸውን የገለጹት በሾኔ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 01 ነዋሪው አቶ ወልዴ ማሞ ናቸው።

ሰርተው በሚያገኙት ገቢ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመምራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የአካባቢያቸውን ገጽታ ስለሚቀይር ለስኬታማነቱ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም