ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ዓለም እውቅና እንዲሰጠው እንሰራለን

ሀምሌ 17/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በዓለም መድረኮች ተገቢው እውቅና እንዲሰጠው በትኩረት እንደሚሠሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎች ገለጹ።

የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ያላቸውን ድርሻ እንዲቀንሱና በአረንጓዴ ልማት ላይ እንዲሳተፉ ታዳጊ ሀገራት በአንድ አቋም ግፊት እንዲያደርጉም ይቀዋል።

ኢትዮጵያ ዓለምን እየፈተኑ ያሉ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ከፍተኛ ሙቀትና የበረዶ ግግር መቅለጥ፣ ሰደድ እሳት፣ አውሎነፋስና ማዕበልን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን በአንድነት ለመቋቋምና ለመከላከል እንዲሰራ በተለያዩ መድረኮች አቋሟን ስታራምድ ቆይታለች።

በተለይ በካርበን ልቀት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውና በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ድጎማ እንዲያደርጉና ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን እንዲቀንሱ ተሟግታለች።

በዚህም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የተለያዩ ስምምነቶች እንዲደረጉና ወደ ተግባር እንዲለወጡ የበኩሏን እየተወጣች ነው።

በተግባርም ከገጠር እስከ ከተማ ህዝቡን በነቂስ በማሳተፍ የአካባበቢ ጥበቃ ሥራዎች እያከናወነች ነው።

በዋናነትም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 18 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የበኩሏን እየተወጣች ነው።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ከሦስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎች ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የአረንጓዴ ልማት ለሌላው የዓለም ክፍል ተምሳሌት ይሆናል ነው ያሉት።

የአናዶሉ ዜና አገልግሎት የኢትዮጵያ ወኪል አዲስ ጌታቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዝቡን በነቂስ በማሳተፍ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ልማት ኢትዮጵያ ለዓለም አካባቢ ጥበቃ የምታደርገውን ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያሳይ ነው ይላል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ አስታርቃቸው ወልዴ ያደጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን እያባባሱ መሆኑን ገልጾ፤ የጉዳቱ ቀጥተኛ ሰለባዎች ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት መሆናቸውን ተናግሯል።

በመሆኑም ያደጉ ሀገራት የበካይ ጋዝ ልቀትን እንዲቀንሱና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች እንዲረባረቡ የታዳጊ ሀገራት በአንድ ድምፅ ግፊት ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ላይ እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖ ተከትሎ ሌሎች ሀገራትም ወደ አረንጓዴ ልማት እንደሚገቡ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ጎረቤት ሀገራትም የአረንጓዴ ልማትን እንዲተገብሩ በመርሃ ግብሩ በማሳተፍ ላይ መሆኗን በማንሳት፤ ይህም ጉዳዩን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት እንዲኖረው ያደርጋል ነው ያለው።

የአየር ንብረት ለውጥ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ለተለያዩ ሠው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እያጋለጣት መሆኑን የጠቀሰው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋቢው አልዓዛር ታደለ ነው።

ሀገራትም ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ዋነኛ አጀንዳ እያደረጉት መሆኑን ያነሳል።

ኢትዮጵያ በስብስባዎች አቋሟን በማራመድ የተለያዩ ስምምነቶች እንዲደረጉ ካላት ሚና ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ መሆኗንም ነው የጠቀሰው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተሠራ ያለው ሥራ በሚገባው ልክ ዓለም አጀንዳ እንዲያደርገው አልተሠራም ያለው ጋዜጠኛ አልዓዛር፤ ኢትዮጵያ ዓለም ንጹህ አየር እንዲተነፍስ የምታደርገውን ጥረት እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብሏል።

በዚህም ረገድ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ሚና በማጉላት በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎቿ በዓለም መድረኮች  ተገቢው ክብርና እውቅና እንዲሰጣት መሞገትና መረጃ ማጋራት እንዳለባቸውም ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም