የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነን- የፖሊስ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነን- የፖሊስ መኮንኖች
ሀምሌ 16/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የህዝቡን ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የፖሊስ መኮንኖች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማ እና ሰርተፍኬት 1 ሺህ 631 ፖሊሶችን አስመርቋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ወንጀልን መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ መመርመር የሚያሥችል ጥልቅ እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ዜጎችን በታማኝነትና በቅንነት ለማገለገል መዘጋጀታቸውን ገልጸው የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የዜጎች መብት መከበር፣ ሰላምና ደህንነታቸው እውን መሆን ለፖሊስ ትልቁ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው ለአገር ዘላቂ ሰላም ከህዝቡ ጋር በትብብር ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገት ጎዳና እንዲፋጠን የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ በየትኛውም መልኩ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ ወንጀልን በጋራ ከመከላከል አንጻር ህብረተሰቡም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡