ቀጥታ፡

ለኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ አቀባበል በነቀምቴ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

ነቀምቴ መስከረም 5/2011 በአዲስ አበባ  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/  መሪ ዳውድ ኢብሳ አቀባበልን በማስመልከት ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ወለጋ ስታዲዮም ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ፡፡ ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ብቂላ በሰጡት አስተያየት መንግስት ከተፎካካሪ  ፖለቲካ ፓረቲዎች ጋር በፈጠረው  እርቅ መሰረት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወደ ሀገር ገብቶ  በሰላማዊ መንገድ ትግል ለማድረግ መወሰኑ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም መንግስት በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋቱ  ማሳያ ነው ብለውታል ፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት የነቀምቴ ከተማና አከባቢዋ ነዋሪዎች ሳይለያዩ  የግል ሥራቸውን በመተው ለአቀባበሉ ያሣዩት የድጋፍ ሰልፍ ለሀገሪቱ አንድነትና ሰላም ከፍተኛ  አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ  አቶ ፍቅሩ ነጋሣ በበኩላቸው መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ  ተፎካካሪ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው ሠላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው እንደሚደግፉና በዚህም መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ለሀገር ግንባታና አንድነት ዋስትና ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ "ከዚህ በኋላ በሀገሪቱ አንዱ የሌላውን መብት የሚጋፋበትና በጠመንጃ ኃይል ስልጣን መያዝ ሳይሆን ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት በሐሳብ ማሸነፍ ነው"  ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መምህር ቀኖ ዋከኔ ናቸው ፡፡ ለውጡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የፕሬዝደንት ለማ መገርሣ ቲም የፈጠረው  የሀገሪቱ ሕዝቦች ትግል ውጤት  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እነሱም በሀገሪቱ ሰላምና እርቅ እንዲኖር ላበረከቱት አሰተዋጽኦም አመስግነዋል፡፡ የድጋፍ ሰልፉ አስተባባሪ አቶ ዱጋሣ መንገሻ  በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል በተፈጠው እርቅ የግንባሩ  መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ወደ  ሀገር  መግባታቸው ለቄሮዎችና ለድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ  ብለዋል፡፡ ሁሉም በመግባባት፣በመቻቻል፣ እና በፍቅር ለሀገር ግንባታ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋቱ አነግ  ወደ አገር ውስጥ በመግባት ሠላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰኑ ለሀገሪቱ ሠላም ዋስትና ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር የምዕራብ ኦሮሚያ ተወካይ አቶ ደራራ ቴሶ ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም