ቀጥታ፡

በስደት፣ በመከራና በእስር የምንማቅቅበት ዘመን አልፏል - ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ

አዲስ አበባ መስከረም 5/2011 ኢትዮጵያውያን በስደት፣ በመከራና በእስር የሚማቅቁበት ዘመን ማለፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። በውጭ አገር የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ፤ “የስደት፣ የመከራና በእስር ቤት የምንማቅቅበት ዘመን አልፎ ለአገር ግንባታ የምንተጋበት ጊዜ መጥቷል'' ብለዋል። ከረጅም ጊዜ የትጥቅ ትግል በኋላ ወደ አገሩ ለተመለሰው የኦነግ አመራር “እንኳን ደህና መጣችሁ” ያሉት ምክትል ከንቲባው “ከዩኒቨርሲቲ ተባረን ጓደኞቻችን ተገድለው፣ በእስር ማቀውና ከአገር ተሰደው ያመጡት የለውጥ ቀን ላይ ደርሰናል'' ብለዋል። በአገሪቱ የመጣው ለውጥ የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋትነት የከፈሉበት እንደሆነ ገልጸዋል። ታጋዮች ቤት ንብረታቸውን፣ ኑሯቸውን ጥለው በጎረቤት አገሮች በረሃ ሲንከራተቱ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው፣ አሁን የአገር ግንባታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት ጊዜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል። “ለዛሬው ነጻነት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መስዋዕትነት ከፍሏል'' ያሉት ኢንጅነር ታከለ በተለይም ወጣቱ ኃይል የማይተካ ሚና እንደተጫወተ አውስተዋል። ''አቶ ዳውድ እንደማንኛችንም ተምረው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቤተሰብ አፍርተው መኖር እየቻሉ ለህዝብ ክብር ብለው ዕድሜያቸውን መስዋዕት አድርገዋል'' ያሉት ኢንጂነር ታከለ፤ ወጣቱ ለፍቅርና ለአገር ግንባታ ጽናትን ከአቶ ዳውድ መማር እንዳለበት አስገንዝበዋል። "እኛ የአባ ገዳ ልጆች ነን"  ያሉት ምክትል ከንቲባው “የአባ ገዳ ልጅ ደግሞ አቃፊ ነውና ሁሉንም የአገራችንን ህዝቦች በፍቅር አቅፈን በጋራ አገር እንድንገነባ አደራ እላለሁ'' ብለዋል። ዛሬ የመጣውን ሰላም ሁላችን ተስማምተን በጋራ መጠበቅና በአንድነት መምራት እንደሚያስፈልግም ኢንጅነር ታከለ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም