ቀጥታ፡

በወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ችግሮች ውስጥ ሆነን ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባን መሆናችንን ያሳየንበት ነው-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ሐምሌ 16 ቀን 2014(ኢዜአ) በ2014 በጀት አመት በወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ችግሮች ውስጥ ሆነን ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባን መሆናችንን ያሳየንበት ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀን “የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ምርት ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት፣ እውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል።

በመድረኩም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፣ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ሀገር ላኪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ለውጡን ተከትሎ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሻሻል የሪፎርም ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ከዓለም ንግድ ስርዓት ውስጥ ተገቢው ስራ እንዲኖረው ለማስቻል በየዘርፉ ከሚያስልጉ ፖሊሲ ከመቅረፅ ጀምሮ የተለያዩ ንቅናቄዎች መደረጋቸውን ገልፀዋል።

በዚህም ለበርካታ አመታት ሲሰራበት የነበረውን የንግድ ህግ የማሻሻል ስራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ ሆኖ እንዲወጣ መደረጉን አንስተዋል።

የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ በአለም መድረክ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ከማሳደግ በላይ በችግሮች ውስጥ ሆኖም ጠንካራና የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል።

በቀጣይም እምቅ ሀብቶችን በመጠቀም የውጭ ዕዳን እንዲቀንስ እና ኢኮኖሚው እንዲዳብር ውጤታማ አስራር ይከተላል ብለዋል።

በ2014 በጀት አመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲኖር ጥረት ያደረጉ አካላትን አመስገነዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 12 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይህ አፈፃፀም ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ብልጫ እንዳለው በመግለፅ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልፀዋል።

ለተመዘገው ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ የመንግስት ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ የበኩላቸውን ሚና እንደተወጡ ተናግረው በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ላኪዎች በበኩላቸው በቀጣይ የበለጠ ለመስራት እንዲሁም በግልፀኝነት እና በታማኝነት ለማከናወን ሽልማቱ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀን “የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ምርት ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት የእውቅና እና የሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም