የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎች በአረብኛ ቋንቋ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ጋዜጠኞች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎች በአረብኛ ቋንቋ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ጋዜጠኞች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ሀምሌ 16/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎችና የልማት አቅጣጫዎች በአረብኛ ቋንቋ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ጋዜጠኞች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከአልጀዚራ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአረብኛ ቋንቋ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ሲሰጥ የቆየውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ትላንት አጠናቋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ- ምግባርን ባከበረ መልኩ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎች ለዓለም ማስተዋወቅ አለባቸው።
የስልጠናው ዋና ዓላማ በአረብኛ ቋንቋ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፤ የዜና ምንጫቸውን በሚገባ እንዲያውቁና የመረጃዎችን ትክክለኛነት አጣርተው እንዲዘግቡ የሚያደርግ ነው።
ጋዜጠኞቹ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ የሚገነቡና የልማት አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ ዘገባዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የአልጀዚራ ሚዲያ ኢንስቲትዩት የሰጠው ስልጠና ጋዜጠኞች ስለ ዜና አፃፃፍ ያላቸውን ልምድ እንዲያጎለብቱ ከማድረግ ባለፈ በተሻሉ ስራዎች አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ያግዛቸዋል ብለዋል።
የአልጀዚራ የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ተወከል በበኩላቸው፤ ስልጠናው ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ በመዘገብ ለቋንቋው ተናጋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ድልድይ እንዲሆኑ፣ የህዝብን እና ሀገርን ጥቅም እንዲያስከብሩና በሙያቸው አገርን እንዲያስተዋውቁ እንደሚያግዝም እንዲሁ።
በስልጠናው የተሳተፉ ጋዜጠኞች በበኩላቸው፤ ስልጠናው የነበረባቸውን ክፍተቶች የሚሞላና በተለይም ለቋንቋው ተናጋሪዎች ሙሉ መረጃ እንዲያደርሱ የሚያግዝ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ስለ ዜና አፃፃፍ ያላቸውን ክህሎትና አጀንዳ አመራረጣቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ ስልጠና ማግኘታቸውንም ነው የጠቀሱት።