በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በግቢው የጓሮ አትክልት በማልማት በከተማ ግብርና አሻራውን እያሳረፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በግቢው የጓሮ አትክልት በማልማት በከተማ ግብርና አሻራውን እያሳረፈ ነው
ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በግቢው የጓሮ አትክልት በማልማት በከተማ ግብርና አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኤምባሲውና በአምባሳደሩ የመኖሪያ ግቢ የሚገኘውን የጓሮ አትክልት ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ “ምግቤን ከጓሮዬ” በሚል መርሃ ግብር ያስጀመሩት የጓሮ አትክልት ልማት በተለያዩ ተቋማት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤምባሲዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ተቋማት በግቢያቸው ባሉ ክፍት ቦታዎች የጓሮ አትክልት እንድያለሙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
የእስራኤል ኤምባሲም ጥሪውን ተከትሎ በግቢው የሚገኙ ክፍት ኮረብታማ ስፍራዎችን በተለያዩ የጓሮ አትክልት እያለማ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ተክሎች፣ በየጊዜው ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች በግቢው ውስጥ እየለሙ ነው።
በኢምባሲው ቅጥር ግቢ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ በቆሎ እና ሌሎችንም የግብርና ውጤቶች በማልማት ላይ ነን ብለዋል።
በመሆኑም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግቢውንና አካባቢውን በማልማት አንድም በምግብ ራስን መቻል በሌላ በኩል አረንጓዴና ውብ አካባቢን መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት።
በእስራኤል የከተማ ግብርናና የጓሮ አትክልት ልማት ተዘውታሪ ተግባር መሆኑን ገልጸው ኤምባሲው የሀገረ እስራኤልን ልምድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጥሪ ጋር በማጣጣም እየተገበረ ነው ብለዋል።
የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፤ ሁሉም ዜጎች፣ መንግስታዊና ያልሆኑ ተቋማት አካባቢያቸውን፣ የመኖሪያና የመስሪያ ቦታቸውን በምግብ ተክሎች እንዲያለሙ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የእስራኤል ኤምባሲም ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሰፋፊ ግቢ ያላቸው ተቋማትም ለጓሮ አትክልት ልማት ትኩረት በመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ ማሳካት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ በልማቱ ላይ ከተረባረቡ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚችሉም ነው የገለጹት።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ የኤዥያ-ፓስፊክ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ፤ በእስራኤል አምባሳደር መኖሪያ ግቢ እየተካሄደ ያለው የጓሮ አትክልት ልማት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የኤምባሲው ሠራተኞች ትኩስና ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን ከጓሯቸው እንዲጠቀሙ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ኤምባሲዎች የያዙትን ሰፋፊ ቦታ ለጓሮ አትክልት ልማት እንዲያውሉት ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም ምግብን ከጓሮ በማምረት በመዲናዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት ያስችላቸዋል ነው ያሉት።