ከክረምቱ ጋር ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ስጋቶች ምንድን ናቸው? - ኢዜአ አማርኛ
ከክረምቱ ጋር ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ስጋቶች ምንድን ናቸው?

የክረምት ስሜቱና ትዕይንቱ ደብዛዛ ነው። ቅሉ የክረምት ወቅት ለሕይወታዊያን የሕልውና ዑደት መሰረት ነው። የበጋ ወራት ፍስሐና ተድላ ኩነቶች የክረምት ስጦታዎች ናቸው። ዘመነ ክረምት ሰማዩ ዝናብ ይለግሳል፤ መሬትም ረስርሳ ሕይወት ትሰጣለች። የሰው፣ እንስሳትና እጽዋት ቀጣይነት በክረምት ይወሰናል። የሰብል ብቅለት፣ የኃይል ማጠራቀሚያ... ጊዜ ነው።
ክረምት ከሌሎች ወቅቶች በደብዛዛ ድባቡ ይገለጻል፤ ኪነ-ጥበብ ክረምትን ጉዞን ይገታልና በናፍቆት፣ ሙቀትን ያስናፍቃልና በቁር፣ ፀሐይን ይከልላልና በብርድ ትገልጸዋለች።
ክረምት ወለድ የሕይወታዊያን ጸጋዎችን ያጎናፅፍ እንጂ የጤና ስጋቶችንም ይወልዳል። በክረምት የምድር ሕይወት መሰረት የሆነን ዝናብን ቢቸርም ዝናብን ፍሰት የሚታከኩ ጎርፍና ውሃ ሙላት ስጋቶች አሉ። እናም ክረምት ጉንፋን መሰል የጤና ችግሮች እየወለደ ለበርካቶች ጤና እክል ይዞ ይመጣል።
በገጠርም ሆነ በከተሞች ውሃ ያቆሩ ሥፍራዎች የወባ ትንኝ ያራባሉ። የውሃ መፋሰሻ ቱቦዎች መዘጋጋት ለኮሌራ በሽታ መንስኤ መሆኑ እሙን ነው። የክረምት ባህሪ እንደ ጉንፋን፣ የአፍንጫ አስም፣ ሳይነሳይትስ አስም፣ ሃይፐርሊን፣ ሲቲቪቲ፣ ኒምናይትስ እና አለርጂ ሳቢያ የሚከሰቱ የመተንፈሻ አካላት የጤና ችግሮችን ይወልዳል።
የክረምት ወራት በተላላፊ በሽታዎች ብቻ አይወሰንም። የክረምት ክፋቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንም መስፋፋት እድል መፍጠሩ ነው። የካንሰር፣ የልብና ስኳር በሽታዎች ተላላፊ ካልሆኑ /ኢ-ተላላፊ/ በሽታዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኮልስትሮል፣ የልብና የተለያዩ የካንሰር አይነቶች በኢትዮጵያ በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑንም የጤና ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
በኢ-ተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ በየዓመቱ ዓለም ላይ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሕልፈተ-ሕይወት እንደሚዳረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት በተለይም በክረምት ወቅት ጤነኛ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ለኢ-ተላላፊ በሽታዎች ያጋልጣሉ።
በየካቲት 12 ሆስፒታልና ሚሊኒየም ኮሌጅ አጠቃላይ ሐኪም ዶክተር ሐብታሙ መንጌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢ-ተላላፊ በሽታዎች ላይ በኢትዮጵያ ሰፊ ጥናት ባይደረግም ወደ ሕክምና ተቋማት የሚመጡ በበሽታው የተያዙ ሕሙማን ቁጥርና ሥርጭት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትሉ ይናገራሉ። በተለይ የደም ግፊት፣ የስኳር፣ ኮልስትሮል፣ የልብና የተለያዩ የካንሰር አይነቶች ሕብረተሰቡ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግባቸው ይገባል ባይ ናቸው።
በክረምት ወቅት በርካታ ሰዎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ በቤታቸው እንደሚያሳልፉ በመግለጽ፤ ይህም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የማጋለጥ ሳይንሳዊ መሰረት እንዳለው ያትታሉ። አንድ ሰው "በቀን ከ30 ደቂቃ ያላነሰ እንቅስቃሴ ቢያደርግ በተወሰነ መጠን ላብ እንዲወጣ በማድረግ ብቻ የቅባት መጠን መቀነስ ስለሚያስችለው ስኳር፣ የደም ግፊት፣ በልብ በሽታ የመጠቃት ዕድሉን ማጥበብ ያስችለዋል" ይላሉ ዶክተር ሐብታሙ።
በአመጋገብ ረገድ ደግሞ ስጋ፣ ወተት፣ እንቁላልና መሰል የእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦችን መቀነስ እንደሚገባ ይመክራሉ። ይልቁንም አትክልትና ፍራፍሬ ምግቦችን መመገብ የተሻለ አማራጭ ነው።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ክረምት የእረፍት ጊዜያቸው እንደሆነ ተማሪዎችና መምህራን ለአብነት ይጠቅሳሉ። ክረምቱ ለእንቅስቃሴ ምቹ ባለመሆኑ በእረፍት ጊዜያት ረዥም ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጥ ከእንቅስቃሴ ጉድለት ጋር ተያይዞ ለሚወለዱ ደም ግፊትና መሰል የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ አብራርተዋል።
”በክረምት ብዙ ሠራተኞች ከቅዝቃዜም ከዝናብም አንጻር ተሰባስበው የመቀመጥ ልምዱ ከፍ ቢልም በአንጻሩ ለተላላፊም ሆነ ለኢ-ተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልም ከፍ ይላል" ይላሉ፡፡
እናም በክረምቱ ለኢ-ተላላፊ በሽታዎች ላለመጋለጥ እንቅስቃሴ ማዘውተር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ከወባ፣ ኮሌራና መሰል ተላላፊ በሽታዎች ለመዳን ደግሞ ለንጽህና ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ይመክራሉ።