ቀጥታ፡

እስራኤል የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመደገፍ አጋርነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች- በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር

ሀምሌ 15/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመደገፍ እስራኤል አጋርነቷን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ እና የሰላም ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በኤምባሲው ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም፤ ኢትዮጵያእና እስራኤል የቆየ ታሪክና ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን አውስተዋል።

ኢትዮጵያና እስራኤል በሰላም ግንባታ ዙሪያ አብረው እየሠሩ ሲሆን ሰሞኑን ኤምባሲውና ሚኒስቴሩ ባደረጉት ውይይት የእስራኤል መንግስት ለኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹንም አስታውሰዋል።

የሁለቱ አገሮች ትብብር በተለያዩ የልማት ስራዎችና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር እስራኤልም የምትታወቅ መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱ ሀገራት በሁሉም መስክ ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ ኤምባሲው ከዚህ ቀደምም የችግኝ ተከላ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው ዘንድሮም ማስቀጠሉን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በኢምባሲው ቅጥር ግቢ የተተከሉ ችግኞችም ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የፍራፍሬ ተክሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚደነቅና ግሩም"  ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እስራኤል የበኩሏን ትወጣለች ነው ያሉት።

ኤምባሲው ሌሎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎች የአረንጓዴ አሻራውን እንዲደግፉ አርዓያ ሆኖ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ በኢምባሲው የተከናወነው የችግኝ ተከላ እስራኤል ለኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን ያሳያል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ እየመጣ ያለውን ተፅዕኖ መቋቋም የሚቻለው በጋራ በመሆኑ የሰላም ሚኒስቴር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን ከሰላም ግንባታ ጋር አስተሳስሮ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ሚኒስቴሩ የአረንጓዴ አሻራውን በማሳረፍ ላይ ሲሆን በቅርቡም በአዲስ አበባ የችግኝ ተከላ ያካሂዳል ሲሉ ጠቁመዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ እንዲሁም የተቋማቱ አመራርና ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም