ቀጥታ፡

በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ 25 ሚሊዮን ዶላር ተዘጋጅቷል

ሀምሌ 15/2014/ኢዜአ/ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥማቸውን የግብዓት አቅርቦት ችግር  ለመቅረፍ 25 ሚሊዮን ዶላር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2015 እቅድ ላይ ከዘርፉ የክልል ቢሮዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በሐዋሳ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው ፡፡

የኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተለያዩ እድሎች  እየተመቻቹ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ አስፈጻሚና ባለድርሻ አካላት  በቅንጅት እንዲሰሩና  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች ይህንን እድል እንዲጠቀሙበት ክልሎች መስራት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት ኢንተርፕራይዞች በብቃታቸው እንደሚወዳደሩና እንደሚሸለሙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ኢንተርፕራይዞች ከአሁኑ ጀምሮ ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚሆን የስራ ማስኬጃ ብድርና 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የካፒታል እቃ ፋይናንስ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢንተርፕራይዞች በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በቀጣይ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፀው  መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የማምረቻ ቦታ ለማቅረብም በጥናት የታገዘ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትና የክልሎች የበጀት ዓመቱ እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የሚካሄድበት ሲሆን በነገው ፕሮግራም የእቅድ ስምምነትና የእውቅና ፕሮግራም እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም