ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለሥራ ፈጠራ እድል አድርገው ሊጠቀሟቸው ይገባል--ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለሥራ ፈጠራ እድል አድርገው ሊጠቀሟቸው ይገባል--ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች
ሐምሌ 14/2014 (ኢዜአ) ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለሥራ ፈጠራ እድል አድርገው ሊጠቀሟቸው እንደሚገባ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሚዘጋጀው ወርሀዊው አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ የውይይት መድረክ "ወጣቶች የነገዋ ኢትዮጵያ መሐንዲሶች" በሚል ርዕስ ዛሬ ተካሂዷል።
ውይይቱ በዋናነት ወጣቶች ተግዳሮቶችን ተቋቁመው በሥራ ፈጠራ ሀገራቸውን ለማሳደግ እንዲሰሩ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያለመ ነው።
በውይይቱ በተለያዩ ዘርፍ የተሠማሩ ሥራ ፈጣሪዎች ያለፉበትን የህይወት ተሞክሮ አካፍለዋል።
ወጣት ሚስጥር ጎሳዬ የቤትና ቢሮ እቃዎችን ማምረት ላይ የተሰማራች ሥራ ፈጣሪ ስትሆን፤ የአካባቢዋ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን የቤት እቃ ለማግኘት ያጋጥማቸው የነበረው የአቅርቦት እጥረት ወደ ሥራ ፈጠራ እንድትገባ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡
በተመሳሳይ በማዕድን ዘርፍ የተሰማራችው ወጣት ብሌን የኔዓለም፤ ለማዕድናት ያላት ዝንባሌና ፍቅር ወደ ሥራ ፈጠራ እንድትገባ እንዳነሳሳት ትገልጻለች፡፡
በሂደትም ከገንዘብ እስከ መሥሪያ ቦታ እጥረት ቢያጋጥማቸውም ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ ዛሬ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የፕላስቲክ ቧንቧና ሌሎችም ምርቶችን በማምረት ወደ ቢዝነሱ የተቀላቀለው ወጣት አዲሱ ባዬ እና ቲማቲምን እንዳይበላሽ የሚያደርግ ኬሚካልን ከማዘጋጀት ተነስቶ በአሁኑ ወቅት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ባለቤት የሆነው ወጣት ጌታቸው ድንቅነህም በመድረኩ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ወጣት አዲሱ እና ጌታቸው እንደሚሉት የሥራ ፈጠራ ሀሳባቸውና የሥራ ውጤታቸው በቤተሰቦቻቸው ጭምር ተቀባይነት ቢያጣም በፅናት በመጓዛቸው ዛሬ ከቤተሰብ አልፎ ሀገር የሚጠቅም ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ከራሳቸው አልፎ ለሀገራቸው ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።
ባለሃብቶች ሥራ ፈጠራን በማበረታታት ረገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሬህይወት አለማየሁ እና በቴክኖሎጂ የሥራ ፈጠራ የተሰማሩት አቶ ማርቆስ ለማ ወጣቶች የነገይቱ ኢትዮጵያ መሐንዲሶች እንዲሆኑ ከባህል ጀምሮ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።
የሀሳቦች ባንክ ማቋቋም፣ ሀሳቦችን ወደ ተግባር መለወጥና ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ መሰረተ-ልማትን ጨምሮ አስፈላጊ ሁኔታዎችን መዘርጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ኢትዮጵያ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍም ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል እየቀየረች ነው ብለዋል።
በተለይም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጀምሮ ያሉ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ፈተናዎችን ተቋቁመው በሀገሪቱ በርካታ የሥራ እድል በመፍጠር ላይ ናቸው ብለዋል።
አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች በየአካባቢው እየፈለቁ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ሥራ ፈጣሪዎችና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆኑ የያዘውን ግብ የሚያሳካ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለሥራ ፈጣሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ከ2 ሺህ 100 በላይ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን በማጠናከር ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የነገዋን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ወጣቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በተለይ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ተወዳዳሪ እና ለሀገር አለኝታ እንዲሆኑ የሥራ ፈጣሪዎች የልማት ኢንስቲትዩት ተቋቁሟል ነው ያሉት።
በፋይናንስ በኩል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር አምስት በመቶውን ለሥራ ፈጣሪዎች እንዲሰጡ ተወስኖ በሕግ መደንገጉን ጠቅሰው፤ ተግባራዊነቱን መንግሥት በትኩረት እንደሚከታተል ጠቅሰዋል።
የጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ማበረታቻ አዋጅ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክ ተናግረዋል።
በቀጣይነት ለሀገር እድገት የሚተጉ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት በቴክኒክና ሙያ የሥልጠና ተቋማት ውስጥ የሥርዓተ-ሥልጠና ክለሳ የተደረገ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።