በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል--- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል--- ሚኒስቴሩ
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በ2014 በጀት አመት ከወጪ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የንግድና ቀጠናዊ ትስሰር ሚኒስቴር አስታወቀ።
በተያዘው 2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢለዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱም ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ የ2014 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ እቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ አርብ የሚያካሂደውን የወጪ ንግድ ቀንን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሻሻል የተከናወኑ መዋቅራዊ ለውጦች ልዩነት ማስመዝገባቸውን አንስተዋል፡
በዚህም የወጪ ንግድ ምርቶችን በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ለማሳደግ በተወሰዱ የፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያዎች ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም ከ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ13 ነጥብ 8 በመቶ እድገት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች መካከል የግብርና ምርቶች 72 በመቶ፣ ማዕድን 14 በመቶ እንዲሁም ኢንዱስትሪ 12 በመቶ የገቢ ድርሻ መያዛቸውን አስረድተዋል።
ከግብርና ምርቶች ቡና ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማስገኘት ትልቁን ድርሻ ወጪ ንግድ በመጠንና ገቢ መጨመሩን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
በተያዘው 2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢለዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስሰር ሚኒስቴር እድገት እያሳየ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታትና ለመደገፍ ብሔራዊ የወጪ ንግድ ቀን ለማክበርና እውቅና ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ነው የገለጹት፡፡
መርሃ ግብሩም "የባለ ልዩ ጣዕም የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል በቀጣይ አርብ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በላኪዎች መካከል የውድድር መንፈስ ለመፍጠር፣ አዳዲስ የገበያ እድሎችን መፍጠር፣ ለገዥ አገሮች የኢትዮጵያን ምርት ማስተዋወቅ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ቀን ዓላማዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ለገበያ የተዘጋጁ ምርቶችን ወደ ውጭ የሚላኩበትን መንገድ ማመቻቸት፣ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ላኪዎችን እውቅና መስጠትም በመርሃ ግብሩ ተካቷል።
ከ25 ሚሊዮንና ከዛ በላይ ዶላር በማስገኘት ከ1 እስከ 3 ደረጃ የያዙ ላኪዎች እውቅናና ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን አጠቃላይ ከላኪዎች ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ 1 እስከ 3 ደረጃ ለያዙት የተለየ እውቅና ያገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም 12 የኤክስፖርት ምርቶች ከ60 በላይ የሚሆኑ አቅራቢዎች የሚሳተፉበት አውደ ርዕይም "የባለ ልዩ ጣዕም የኢትዮጵያን ይግዙ" ቀን ላይ እንደሚቀርብ ተገልጿል።