ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሠላም ጥረቶች የሚያበረታቱ ናቸው- በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ

ጎንደር፤ ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሠላም ጥረቶች የሚያበረታቱ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን ገለጹ።

ጉዳይ አስፈጻሚዋ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ በሽመላኮ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ትናንት ከጎበኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ መንግሥት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ያደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ ከ2 ሚሊዮን በላይ  ተፈናቃይ ወገኖች መድረሱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የተጀመሩ የሠላም  ጥረቶች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሀገራዊ ምክክሩንና የሰላም አማራጩን በአብነት አንስተዋል።

ጉዳይ አስፈጻሚዋ ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ ሀገራዊ ምክክሩ  በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ  ውጤታማ እንዲሆን አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

ትሬሲ አን ጃኮብሰን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም  ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታዎች ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆኑ የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚበረታቱና በበጎ ጎኑ የሚታዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ጉዳይ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት እስካሁን 660 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ቀርበዋል።

በተለይ በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ባለፈው ዓመት ብቻ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች  ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰተው የድርቅ ችግር ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ትሬሲ አን ጃኮብሰን በመጠለያው ከሚገኙ የተፈናቃይ ተወካዮች ጋር  ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይም የመከሩ ሲሆን፤ በጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራሞች እንዲመቻቹ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በሽመላኮ መጠለያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው የመጡ ከ2 ሺህ በላይ ወገኖች ከነቤተሰቦቻቸው ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም