በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል
ሐምሌ13 ቀን 2014 (ኢዜአ)በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ በጅምላ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ደንበኞች ያቀርባል።
በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመትም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች፣ እንዲሁም ለሱዳንና ጅቡቲ ኃይል በሽያጭ በማቅረብ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ ተናግረዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 9 ሺህ 472 ጊጋ ዋት ማቅረቡን ገልፀው፤ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የእቅዱን 90 በመቶ እንዲሁም ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የእቅዱን 116 በመቶ ኃይል ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲ 527 ጊጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ አቅዶ 611 ጊጋ ዋት ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ለሱዳን ደግሞ 1 ሺህ 93 ጊጋ ዋት በሰዓት አቅርቧል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት 12 ሺህ 30 ጊጋ ዋት ኃይል ማቅረቡንም ተናግረዋል።
ተቋሙ ለጅቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ነው የገለፁት።
ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም የ5 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካቀረበው ኃይል 11 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ደግሞ 364 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ተናግረዋል።