የከተማ አስተዳደሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሰላም ግንባታ እየሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው - ትሬሲ አን ጃኮበሰን - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ አስተዳደሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሰላም ግንባታ እየሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው - ትሬሲ አን ጃኮበሰን
ጎንደር ሀምሌ 13/2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሰላም ግንባታ እየሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ገለጹ።
የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምከትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ጋር በሰላምና በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዩች ላይ በጎንደር ከተማ ተወያይተዋል።
ጉዳይ አስፈጻሚዋ ከውይይት በኋላ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ደረጃ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።
በሀገር ደረጃ የሚካሄደው ምክክርና የሰላም ንግግሮች ሰላምን በማረጋገጥ በኩል የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
በጎንደር ያለው ታሪካዊና የአለም ቅርስ የሆነውን ቤተመንግስትንና የተለያዩ ባህልና ሃይማኖት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሰላምና በጋራ የሚኖሩበት መሆኑ እንዳስደነቃቸው ነው የተናገሩት።
አስተዳደሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሰላም ግንባታ እየሰራ ያለውን ተግባር በተቀዳሚ ከንቲባው ከተደረገላቸው ገለጻ መረዳታቸውን ጠቅሰው ተግባሩ የሚበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሰላም ግንባታ የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ አስተዳደሩ በብሄራዊ ምክክሩ ላይ የሚጠበቅበትን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ከገለጻው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
በትምህርትና በጤና ዙሪያ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰሩም ነው የጠቀሱት።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው ሰላምን ለማረጋገጥ በአስተዳደሩና በህብረተሰቡ ትብብር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር መንግስት ያቀደው ብሄራዊ ምክክር እንዲሳካ የከተማው ህዝብ በሚያደርገው ተሳታፎ ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የጎንደር ከተማ ከአሜሪካ ከተሞች ጋር ያለው የእህትማማችነት ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢምባሲው ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚዋ የተመራው ልዑክ በሰሜን ጎንዳር ዞን ዳባት ከተማ በሽምላኮ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል።