ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እንደገለጸው ካለው የስደተኞች ቁጥር አንጻር በቂ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉዓለም ደስታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት የመጡ ከ9 መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ አስጠልላለች።
የአትዮጵያ መንግስትም ለእነዚህ ስደተኞች አካላዊ ጥበቃን ጨምሮ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት አመቻችነት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ስደተኞች ራሳችውን እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ዓለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በዩክሬንና ራሺያ ጦርነት ምክንያት አጋር ድርጅቶች ለስደተኞች የሚያቀርቡት ድጋፍ በግማሽ መቀነሱን አቶ ሙሉዓለም ተናግረዋል።
ሁኔታው ለዓለም ዓቀፍ ለጋሽና ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ትኩረታቸውን ወደ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲቀይሩ አስገድዷል ብለዋል።
በዚህ ወቅትም የስደተኞች ዋነኛ አጋር የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንኳን ለአንድ ስደተኛ በቀን መቅረብ ካለበት 2ሺህ 100 ካሎሪ ምግብ መጠን 50 በመቶውን ብቻ እያቀረበ ነው ብለዋል።
በዚህም ስደተኞች በተቀመጠው ዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ምግብ እያገኙ አለመሆኑን ገልፀው ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለስደተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጨመር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ ማርጋሬት አትኖ፤ ለስደተኞች በቂ ድጋፍ የማቅረብ ችግር መኖሩን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አስታውሰው ለስደተኞች ጥበቃ ለማድረግ አዋጆችን አውጥታ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም መስክረዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞች በመጠለላቸው ምክንያት የተሟላ ድጋፍ ማቅረብ እንዲቻል ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በዋናነት ከኤርትራና ከደቡብ ሱዳን በርካታ ቁጠር ያላቸው ስድተኞች መጠጊያ መሆኗ ይታወቃል።