ቀጥታ፡

የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር ለመደገፍ በሶስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ስምምነት ተደረገ

ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር ለመደገፍ በተለያዩ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በጋራ ለመስራት ስምምነት ተደረገ።

ተቋማቱ ጥናትና ምርምሩን የሚያስተባብር የጋራ ግብረ-ሀይል ማቋቋማቸው ተገልጿል፡፡

ግብረ-ሀይሉን ያቋቋሙት የኢትዮጵያ፣ የዩጋንዳና የሩዋንዳ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ በአፍሪካ የሚከሰቱ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈታ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እገዛ ያደርጋሉ።

የጋራ ግብረ-ሀይሉን ያቋቋሙት ከኢትዮጵያ የጎንደር፣ ከዩጋንዳ የማኬሬሬ እና ከሩዋንዳ የኪጋሊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ ተቀማጭነቱ ደቡብ አፍሪካ የሆነው ፎርት ሀሬ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ስራውን ያስተባብራል።

ተቋማቱ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ፎርት ሀሬ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ብሔራዊ ፋውንዴሽን ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዊሊ ቺንያሙሪንዲ በሰጡት መግለጫ፤ ስምምነቱ በጥናትና ምርምር፣ በትብብር መማማር፣ በአዳዲስ ሥርዓተ ትምህርት ልማት፣ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማር እና የአጫጭር ስልጠናዎች በመስጠት በኩል በትምህርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንድናመጣ ያግዘናል ብለዋል።

በትምህርት ዘርፉ በትብብር መስራት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ዋና ብልሃት ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ዊሊ ቺንያሙሪንዲ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም