የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል መድሃኒት በምርምር ማግኘታቸውን አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል መድሃኒት በምርምር ማግኘታቸውን አስታወቁ
ሀምሌ13/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን ስነ-ህይወታዊ በሆነው ፈንገስ በመጠቀም መከላከል የሚያስችል መድሃኒት በምርምር ማግኘታቸውን አስታወቁ።
ተመራማሪዎቹ ያገኙት ውጤት ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ እጽዋቶችን የሚያጠቃ በሽታን ለመከላከል ከውጭ የምታስገባውን "ትራይኮደርማ" የተሰኘ ፈንገስ መተካት የሚችል መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ምርምሩ ረዥም ዓመት የፈጀ ሲሆን በምርምሩ ላይ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።
መድሃኒቱ ኬሚካል ጥቅም ላይ ሳይውል ፈንገስን በመጠቀም ሌሎች በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
የምርምሩ ሀሳብ አፍላቂ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማይክሮቤል ሴሉላር ሞሎኩላር ባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ተስፋዬ ዓለሙ ናቸው።
ዶክተር ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአገሪቷ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ቡና እንደመሆኑ የተገኘው ውጤት አገራዊ ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
በምርምር የተገኘው ፈንገስ በሽታዎችን ለምግብነት የሚጠቀም መሆኑን የገለጹት ዶክተር ተስፋዬ፤ ከስንዴ ገለባ፣ከወፍጮ ቤት ትራፊ ዱቄቶች እና ጥቅም ላይ የማይውሉ ተረፈ ምርቶች የሚዘጋጅ መሆኑን አብራርተዋል።
የተገኘው መድሃኒት ከቡና ባሻገር ሌሎች የእጽዋት በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል መሆኑን በተደረገው ጥናት መረጋገጡን ጠቁመው፤ ለአብነትም የአበባ በሽታዎችን እንደሚከላከል ተናግረዋል።
የምርምር ውጤቱ ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ እጽዋቶችን የሚያጠቃ በሽታን ለመከላከል ከውጭ የምታስገባውን "ትራይኮደርማ" የተሰኘ ፈንገስ መተካት የሚችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ይህም የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደሚያስችል በመጠቆም፡፡
ተማራማሪው እንደሚሉት፤ መድሃኒቱ የቡና ምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው።
መድሃኒቱ አስፈላጊውን ሂደቶች አልፎ ጥቅም ላይ ሲውል ለአርሶ አደሮች የአጠቃቀም ገለጻ የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል።
በምርምሩ ላይ ከሁለተኛ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የተሳተፉት ዶክተር አፍራሳ ሙላቱ በበኩላቸው የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን ለመከላከል የተገኘው የምርምር ውጤት ሌሎች ምርምሮችን ለማድረግ በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
የቡና ግንድ አድርቅ በሽታ የግንዱን የውስጠኛውን አካል የሚያጠቃ በመሆኑ በጸረ ተባይ ማጥፋት እንደማይቻል የገለጹት ዶክተር አፍራሳ በምርመር የተገኘው ውጤት ግን በተሻለ መከላከል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።