አስተዳደሩ ከ91 በላይ የሚሆኑ በሳይበር እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን አዳዲስ ታዳጊ ወጣቶችን ተቀበለ - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ ከ91 በላይ የሚሆኑ በሳይበር እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን አዳዲስ ታዳጊ ወጣቶችን ተቀበለ
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በ2014 የክረምት መርሃ ግብር ከ91 በላይ የሚሆኑ በሳይበር እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶችን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተቀብሎ የሥልጠና ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ገለጸ፡፡
የማዕከሉ ሃላፊ አቶ ካሳሁን ደሳለኝ እንዳሉት የክረምት ወቅት ትምህርት የሚዘጋበት ጊዜ በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች በመስኩ ካላቸው ልዩ ተሰጥኦ አኳያ በታለንት ማዕከሉ ተቀብለን የሥልጠና ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ ከ6ኛ ከፍል ጀምሮ ከ91 በላይ ተማሪዎች በ2014 የክረምት ወቅት የተቀበላቸውን ጨምሮ ለአራት ዙር ያክል 127 ወንዶች እና 14 ሴቶች በጥቅሉ 141 ባለ ልዩ ተሰጥዖ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት ቴክኒካል ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑም አቶ ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡
የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከሉ የተቀበላቸውን ታዳጊ ወጣቶች ከክህሎት ስልጠናዎች ጀምሮ የቴክኒክ እና ለስራቸው የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሚሰሯቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለመፈተሽና ለመሞከር የሚያስችላቸው ላብራቶሪም በማዕከሉ ውስጥ እንደሚያገኝ ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት ወደ ተቋሙ የታለንት ማዕከል ላልመጡ እና በመስኩ ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን በተመለከተም የቀጥታ መረብ (Online) ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
ተማሪዎች የሚመረጡበት ወይም የሚመለመሉበት መስፈርትም ባዘጋጁት ፕሮጀከት መሰረት ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ በቀጣይም አብዛኛውን ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የቀጥታ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ወደ ሳይበር ታለንት ማዕከል ከገቡ ታዳጊ ወጣቶች መካከል በማልዌር ልማት (Malware Development) ፕሮጀክቱ የተመረጠው የ12ኛ ክፍል ተማሪ አቤኔዘር ሙሉጌታ በሰጠው አስተያየት ባገኘው ዕድል ደስተኛ መሆኑን ጠቅሶ በማዕከሉ እውቀቱን የበለጠ እንዲያዳብር የተሻለ ቴክኒካል ድጋፍ እንደሚደረግለት ተናግሯል፡፡
በተለይም ከዚህ ቀደም ስለ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሰማሁት እና አሁን በቦታው ሆኜ ያየሁት እና እየተደረገልኝ የሚገኘው ድጋፍ በምንም መመዘኛ የማይገናኝ ነው ብሏል፡፡
ሌላዋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ባለ ልዩ ተሰጥዋ ጽናት ዳዊት በበኩሏ በመስኩ ለመሰማራት በነበራት ፍላጎት ወደ ማዕከሉ አቅንታ የተሻለ ድጋፍ እያገኘች ስለመሆኗ ተናግራለች፡፡
የኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በሳይበር ሴኪዩሪቲ እና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ተሰጥዖ ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ክህሎታቸውን ለማሳደግ እና ፕሮጀክቶቻቸውን ለመተግበር የሚያስችል የባለሙያ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተጠቁሟል።
አሁንም ፍላጎት እና ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች በ cychalleng.insa.gov.et ድረ-ገጽ መመዝገብ እንደሚችሉ እንዲሁም ለበለጠ ማብራሪያ በ 0904311833 ወይም 0904311837 መደወል እንደሚችሉ ኃላፊው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ