የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከአካባቢ ጥበቃ በተጓዳኝ የኢትዮጵያዊያንን በትብብር የመስራት ባህል ያጠናከረ ነው-አፈ-ጉባኤ አገኘው ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከአካባቢ ጥበቃ በተጓዳኝ የኢትዮጵያዊያንን በትብብር የመስራት ባህል ያጠናከረ ነው-አፈ-ጉባኤ አገኘው ተሻገር
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከአካባቢ ጥበቃ በተጓዳኝ የኢትዮጵያዊያንን በትብብር የመስራት ባህል ያጠናከረ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘው ተሻገር ተናገሩ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አመራር እና ሰራተኞች ሸጎሌ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሮድካስትቲንግ ኮርፖሬሽን ግቢ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር በዚህ ወቅት እንዳሉት ምክር ቤቱ በተከታታይነት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከአከባቢ ጥበቃ ባሻገር የዜጎችን በትብብር የመስራት ባህል የሚያጎለብት መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በመርሃ-ግብሩ ችግኝ ከመትከል ባሻገር እንዲፀድቁ መንከባከብ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሰሩ ስራዎች የአከባቢ ገጽታን በመቀየር ረገድ ከወዲሁ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዛሕራ ሁመድ እና የምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ዳባ፤ በመርሃ ግብሩ የተከሏቸውን ችግኞችን በመከባከብ ረገድም በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የተቋማቱ አመራር እና ሰራተኞች የኢትዮጵያ ብሮድካስትቲንግ ኮርፖሬሽን በሸጎሌ አካባቢ አዲስ እያስገነባ ያለውን ስቱዲዮ ጎብኝተዋል።