ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የመንግሥት ኩሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ናቸው።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በተለይ በመረጃ ልውውጥ፣ በአቅም ግንባታ እንዲሁም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የሳይበር ደህንነት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሲሆን በአጠቃላይ በዚህ ዓመት አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው ተብሏል።
ዶክተር ለገሰ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመንግስትን ፖሊሲዎች ስትራቴጂ ተግባራትና አፈጻጸሞች በተመለከተ መረጃን የመተንተንና ለህዝብ የማድረስ ኃላፊነትን የዞ እየሰራ ነው።
አገልግሎቱ በህዝቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ወደ አስፈጻሚው አካል የማድረስ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ዛሬ የተፈረመው ስምምነት አገልገሎቱ ያቀዳቸውን ግቦች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሳካት ያስችለዋል ነው ያሉት።
እንደ ሀገር የተቀናጀ የመረጃ ስርጭት እንዲኖርና የህብረተሰብ ፍላጎቶችን ወደ መንግስት ለማድረስ እንዲሁም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለማሟላት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አቅምን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ስምምነቱ መረጃዎች በዲጂታል መንገድ ተሰንደው ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፉና ሁለቱም ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፤ በስምምነቱ መሰረት ኢንስቲትዩቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትን የመረጃ አቅርቦትና የመረጃ ትንተናን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎች ያግዛል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ አዳዲስ የመገናኛ ዘዴዎችን ለመጠቀም እድል የሚፈጥር ስምምነት መሆኑን ተናግረዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከዓለም አቀፍ የዲጂታል ቋቶች የሚገኙ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለአገልግሎቱ እንደሚያቀርብና በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ኃላፊዎቹ አክለውም ስምምነቱ የመረጃ ተደራሽነትን ለማጠናከር የፌደራል ተቋማት በጋራ በመስራት የፌደራል መንግስቱን ዓላማ የሚያሳካና የጋራ አቅምን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን በተለያዩ ዲጂታል አማራጮች ለህዝቡ መረጃ በፍጥነት እንዲያደርስ ከድረገፅ እስከ ዩቲዩብ ደህንነቱ የተረጋገጠ የዲጂታል ማዕቀፍ ለማዘጋጀትም ስምምነቱ መሰረት መጣሉን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤