አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረው የሰላም አማራጭ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረው የሰላም አማራጭ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረው የሰላም አማራጭ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር ገለጹ።
ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሀመር በተያዘው ሳምንት ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገራት እንደሚያቀኑም ተገልጿል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ውይይት አድርገዋል።
የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ብሔራዊ ምክክር፣የሰላም አማራጭ ሂደት፣የኢትዮጵያ ከአፍሪካ የእድገትና የእድል ድንጋጌ(አክት) መውጣትና የ”ኤች አር 6600” እና የ”ኤስ 3199” ረቂቅ ሕጎች የውይይቱ ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አምባሳደር ስለሺ የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር በመሆን በግጭትና በድቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ያልተገደበና ያልተቋረጠ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኑንና ሌሎች ባለድርሻዎችም ለሰላም መምጣት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያና አሜሪካ ካላቸው ታሪካዊ ትብብር አንጻር ኢትዮጵያ ከአጎዋ ማስወጣትና የኤች አር 6600 እና የኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች ማውጣት የመሰሉ በጣም ጎጂ እርምጃዎች አይገባትም የተዘጋጁት ሕጎች መሰረዝ አለባቸው ብለዋል” አምባሳደር ስለሺ።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በበኩላቸው መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ያልተገደበና ያልተቋረጠ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንሚያደንቁና የአሜሪካ መንግስትም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረው የሰላም ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።
የ”ኤች አር 6600” እና የ”ኤስ 3199” ረቂቅ ሕጎች በተመለከተም ረቂቅ ሕጎች በተመለከተ ኮንግረስ አባላት ጋር ውይይት ማድረግና ግንኙነት ማጠናከር ያስፈጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ በድጋሚ ለመመለስ ሟሟላት ያለባትን መስፈርቶች ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በተያዘው ሳምንት በምስራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ እንደ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ማይክ ሀመር በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም አምባሳደር ዴቬድ ሳተርፊልድን ተክተው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ እንዲሆኑ መሾማቸው ይታወሳል።
ማይክ ሀመር በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።
ልዩ ልዑኩ አሜሪካ ሁለት ዓመት ባልሟላ ጊዜ ውስጥ የሾመቻቸው የአፍሪካ ቀንድ መልዕተኛ ናቸው።
ከአምባሳደር ዴቬድ ሳተርፊልድ በፊት ጄፍሬ ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ በመሆን አገልግለዋል።