ጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አዳማ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ የስራ ዘመን አንደኛ ዓመት ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ዛሬ ተጀምሯል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል ሰላም አስተማማኝ ለማድረግና የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ጨፌው ተገቢውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጨፌ ኦሮማያ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገልጸዋል።
የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግና የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን የጨፌ አባላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በተወሰኑ የክልሉ ዞኖች የነበረው “የጸጥታ ችግር” ለመቅረፍ የተጀመረው ስራ “ትርጉም ባለው መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል ማህበረሰብን ያሳተፈ ቡሳ ጎኖፋ(የበጎ አድራጎት ስራ) በማከናወን በቦረና፣ጉጂ፣ ምስራቅ ሐረርጌና ባሌ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማደራጀት የመደበኛ ፍርድ ቤቶች የስራ ጫናን ከማቃለል ባለፈ የፍትህ አገልግሎቱን እንዲቀላጠፍ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት አፈ-ጉባኤዋ።
የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ በሁለት ቀናት ቆይታው የኦሮሚያ ክልል የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስራ ዕቅድ አፈጻጸም፣የ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት የስራ እቅድ ማስፈጸሚያ በጀት፤ የክልሉ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርትና ሹመቶችን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ተገልጿል።